ቀጥታ፡

በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ እያማተሩ በሉዓላዊነታችን ላይ ለሚሰነዘሩብን ጫናዎች እንደማንበረከክ በግልፅ ሊታወቅ ይገባል - አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18 /2013 (ኢዜአ) “በዚህ ወቅት በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ እያማተሩ በሉዓላዊነታችን ላይ ለሚሰነዘሩብን ድፍረት አዘል ጫናዎች እንደማንበረከክ በግልፅ ሊታወቅ ይገባል” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስገነዘቡ።

“የመላው አፍሪካውያን የአንድነት ጥላ ምልክት ለሆነው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአፍሪካ ህብረት) 58ተኛ ዓመት የምስረታ መታሰቢያ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ” ሲሉም ለአፍሪካ ቀን መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው “የአፍሪካ ቀን በየአመቱ ሲዘከር ሃገራችን ኢትዮጵያ ነፃነቷን እና ክብሯን በቀዳሚነት አስጠብቃ መዝለቋ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ደማቅ ታሪካዊ ትርጉም ይቸራል” ብለዋል።

ከ125 ዓመታት በፊት በወራሪ ሃይል ኢትዮጵያን በቅኝ የማሳደር ቀቢፀ ተስፋን ተከትሎ፤ የቁርጥ ቀን ጀግኖች ባደረጉት አኩሪ ተጋድሎ የአድዋ ድል ባለቤት የመሆን ዘለዓለማዊ ዕድል መጎናጸፍ መቻሉን አስታውሰዋል።

“በተለይ ሚያዝያ 27 ቀን 80ኛ ዓመት የድል በዓል ያከበርንበት ታሪካዊ አውድ፤ የኢትዮጵያውያን የጀግንነት ከፍታ የተገለጠበት ተጨማሪ የድል አድራጊነት እሴት አውርሶናል” ብለዋል።

የአፍሪካ ቀንን የሚከበርበት ታሪካዊ ምክንያት እንደ አህጉር በፀረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሎ የተመዘገበትን አኩሪ ድል ለመዘከር እንደሆነ አስታውሰው፤ “መቼም ቢሆን በውጭ ኃይሎች ጫና የማንበርከክ ስለመሆናችን ህልው ማረጋገጫ ነው” ብለዋል።

“በዚህ ወቅት በሃገራችን የውስጥ ጉዳይ እያማተሩ በሉዓላዊነታችን ላይ ለሚሰነዘሩብን ድፍረት አዘል ጫናዎች እንደማንበረከክ በግልፅ ሊታወቅ ይገባል” ያሉት አቶ ደመቀ፤ “በዚህ አግባብ እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድነት፥ በመከባበር እና በአሸናፊነት መርሆዎች በዓለምአቀፍ አውድ በነፃነት እና በተወዳዳሪነት ፀንተን እንቀጥላለን” ሲሉ አረጋግጠዋል።

የድል አድራጊነት ወኔን በማጥበቅ ኢትዮጵያ በመጪው ጊዜያት ለመላው አፍሪካ የነፃነት እና የኩራት ቀንዲል ሆና እንድትዘልቅ በጋራ ርብርብ እንዲደረግ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም