ቀጥታ፡

የችግሮች ሁሉ የመፍቻ ቁልፉ ለሆነው ሰላም ሁሉም አስፈላጊውን ዋጋ መክፍል አለበት...ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18/ 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላሉት ችግሮች ሁሉ መፍትሄው ሰላም በመሆኑ ሁሉም ለሰላም ሲል አስፈላጊውን ዋጋ መክፍል እንዳለበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርሰቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳሰቡ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ መካሄድ ላይ ይገኛል።

በጉባኤው የመክፈቻ መርሃ ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርሰቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በሰው ልጆች ላይ ከበድ ያለ ፈተና እየተከሰተ በመሆኑ ሁሉም ሊጸልይ ይገባል ብለዋል፡፡

የቤተ-ክርስቲያኗ ገዳማትና አድባራት፣ መነኮሳትና ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ወጣቶች እንዲሁም ምዕመናን ፈተና ላይ ሲወድቁ ቅዱስ ሲኖዶሱ በቀጥታ የሚመለከተው በመሆኑ ለመፍትሄው ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት።

በሀገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ጉባኤው በጸሎት፣ በማስታረቅ፣ በቁሳቁስና በመጠለያ እንዲሁም በምግብና መጠጦች ድጋፍ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ላሉት ችግሮች ሁሉ መፍትሄው ሰላም በመሆኑ ሁሉም ለሰላም ሲል አስፈላጊውን ዋጋ መክፍል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂና ዋስትና ያለው ሰላም ለማምጣት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በውይይት፣ በመነጋገርና በመግባባት ለጋራ ሰላም ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ሠላም የህልውና ጥያቄ መልስ በመሆኑ ሁሉም በጋራ እንዲቆምም ፓትርያርኩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በቅዱስ ሲኖዶስ ዓመታዊ ምልዓተ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርሰቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቲያስን ጨምሮ ሁሉም የሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም