የኢትዮጵያ ሣምንት ሀገራችንን ለማወቅ ፈር ቀዳጅ መርሃ ግብር ነው - ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሣምንት ሀገራችንን ለማወቅ ፈር ቀዳጅ መርሃ ግብር ነው - ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
ግንቦት 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) በወዳጅነት ፓርክ የተካሄደው የኢትዮጵያ ሣምንት መርሃ ግብር አገራችንን ለማወቅ ፈር የቀደደ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ሣምንት በሚል ከግንቦት 10 ቀን 2013 ጀምሮ የተካሄደው የባህል፣ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ኤግዚቢሽንና ፌስቲቫል ተጠናቋል።
በማጠናቀቂያ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ዘመናትን ያስቆጠሩ የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብቶች አልተጠቀምንባቸውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሣምንት የባህል፣ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ኤግዚቢሽንና ፌስቲቫል አገራችንን በአግባቡ አውቀናት እንድንጠቀምባት የሚያደርግ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ባለሃብቶች በየክልሎቹ የሚገኙ ሃብቶችን እንዲመለከቱና እንዲያለሙ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁንና የተፈጥሮ ሀብት ስላለ ብቻ ሀብታም መሆንና ከድህነት መውጣት ስለማይቻል ሁሉም በጋራ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ፕሬዚዳንቷ ኢትዮጵያ አሁን ለገጠሟት ችግሮች ዘዴና መላው በእጃችን ያለ መሆኑን አውቀን ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል በመልእክታቸው።
መርሃ ግብሩን ላዘጋጁት የሴቶችና ህጻናት፣ የባህልና ቱሪዝምና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴሮችና ሌሎችም አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳው በበኩላቸው በኢትዮጵያ ሣምንት 'ሕብረ ብሔራዊ የሆነች ኢትዮጵያን በተግባር አይተናል' ብለዋል።
መርሃ ግብሩ የታሰበለትን ዓላማ ያሳካ መሆኑንም ገልጸዋል።
በወዳጅነት ፓርክ በተካሄደው ዝግጅት ሁሉም ክልሎች ባህልና ማንነታቸውን የሚያሳዩ አውደ ርዕዮችና ሀብቶች አስተዋውቀዋል።
መርሃ ግብሩን ህጻናትን ጨምሮ ከ22 ሺህ በላይ ዜጎች ጎብኝተውታል ተብሏል።