ቱሪዝምን በዕውቀት በመምራት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ መስራት ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ቱሪዝምን በዕውቀት በመምራት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ መስራት ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17/2013 ( ኢዜአ) የቱሪዝም ዘርፉን በዕውቀት በመምራት ገቢውን ለማሳደግ በሆቴልና ቱሪዝም ስራ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት እንደሚገባ የሳይንስንና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ አሳሰቡ።
የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ማዕከል ያዘጋጀው 8ኛው የቱሪዝም ሲምፖዚየም "ቱሪዝም ለሠላም፣ ሠላም ለቱሪዝም" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል።
የማዕከሉ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ማዕከሉ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የቱሪዝም ስራ በመስራት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ለዚህ ስኬት ይረዳ ዘንድ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ተቋሙ የበለጠ መስራት አለበት ብለዋል።
ማዕከሉ ለቱሪዝም እድገት አስተዋጽኦ ያላቸው ሁኔታዎችን በማጥናት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ አገር በቀል ዕውቀቶችን ለመተግበር ይረዳት ዘንድ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በማጣመር ተግባር ላይ ለማዋል እየሰራች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።
በመሆኑም የቱሪዝም መስህቦቿን የበለጠ ለማስተዋወቅ በትምህርት የተደገፈ አካሄድ መከተል ይገባል ነው ያሉት።
የቱሪዝም ሃብቶቿን በቴክኖሎጂ በማስተዋወቅ ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግም ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።
ቱሪዝምን የኢኮኖሚ ምሰሶ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት ናቸው።
ማዕከሉ ባህልና እሴትን በመጠበቅና የቱሪስት መስህቦችን በማስፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚያግዙ ባለሙያዎችን ለማፍራት እየሰራ ነው ብለዋል።
በሲምፖዚየሙ የታደሙት መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ የዘርፉ ባለሙያዎች በየአካባቢው ያለውን ሀብት በመጠበቅና ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ መስራት አለባቸው ነው ያሉት።
ደካማ የሆነውን አገራዊ የመጎብኘት ባህል በማዳበር የእርስ በእርስ ትውውቅና ትስስርን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
ቱሪዝም ለሠላም መስፈንና የሕዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነትና ትብበር ለማጎልበት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
አንዱ የሌላውን ባህል እንዲያውቅ በማድረግና አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በመስራት ግጭትን ማስቀረት ይቻላል ብለዋል።