ሀገሪቱን ወደ ታላቅ ከፍታ ለማድረስ አንባቢ ትውልድ ማፍራት ላይ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገሪቱን ወደ ታላቅ ከፍታ ለማድረስ አንባቢ ትውልድ ማፍራት ላይ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
ድሬዳዋ ፤ ግንቦት 17/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ወደ ወደ ታላቅ ከፍታ ለማድረስ የሚሰሩ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ለንባብ የሚተጋና ማንበብን የሚያፈቅር ትውልድ ማፍራት ላይ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብት መጽሐፍት ኤጀንሲ፣ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲና ድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የምንባብ ሣምንት ዛሬ በድሬዳዋ በይፋ ተጀምሯል፡፡
ዝግጅቱ ሲጀመር የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን እንደተናገሩት ፤ ሀገሪቱን ታላቅና የበለፀገች ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት ፍሬ የሚያፈሩት ለምንባብ የሚተጋና ማንበብን የሚያፈቅር ትውልድ ማፍራት ሲቻል ነው፡፡
አንባቢና ተመራማሪ ትውልድ ለማፍራት የሚከፈለው መስዋትነት አገሪቱን ወደ ታላቅና ከፍታ የማድረሱ ግቡ ዕውን ያደርጋል ብለዋል፡፡
አሁን በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የላላ የማንበብ ሂደት ለማሻሻልና የሚፈለገው ትውልድ ለማፍራት ከቤተሰብ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተቀናጀ ሥራ መስራት አለብን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ የተጀመረው የምንባብ ባህል እንዲጎለብት ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታወቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኮኖ አምላክ መዝገቡ ትውልዱ የምንባብ ፍቅርና ልምዱ እንዲያዳብር ኤጀንሲው በተናጠል አካሄድ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በድሬዳዋ የተዘጋጀው የምንባብ ሣምንት ይህንኑ ዓላማ ያነገበና ዓመቱን ሙሉ የማንበብ ዝንባሌና ትውስታ በወጣቱና ሌለው ህብረተሰብ ውስጥ ለመፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።
ድሬዳዋ የህትመት ውጤት በማስገባት የማንበብን ጠቀሜታ አስቀድማ የተረዳች ከተማ መሆኗን የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙራድ በደዌ ናቸው ፡፡
ይህንኑ የቀድሞ ታሪኳን በመመለስ አንባቢና ተመራማሪ ትውልድ ለመፍጠር ቤተ-መጻሀፍትን ተደራሽ መደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ለረጅም ዘመናት በማንበብና በማስተማር ያሳለፉ መምህራን፣ ጋዜጠኞችና ደራሲዎች የማንበብን መሠረታዊነትና ያለውን ጠቀሜታ በዝግጅቱ ላይ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡
ብዝግጅቱ በርካታ የመፅሀፍት ነጋዴዎች መፅሀፍትን ለአንባቢያን በቅናሸ አቅረበዋል፡፡
"መጽሀፍት ለእውቀት ገበታ፣ መዛግብት ለዘመን ትውስታ" በሚል መሪ ሃሳብ በምድር ባቡር አዳባባይ የተጀመረው የምንባብ ሣምንት ዝግጅት በቆይታው የፅሁፍ ቅርስ አውደ ርዕይ፣ የማንበብ ጠቀሜታ ላይ የሚያተኩርና ታዋቂ ምሁራን የሚካፈሉበት የውይይት መድረክ፣ ሀገር አቀፍ እውቅና ያተረፉ ወጣቶች የሚሳተፉት የኪነ-ጥበብ ምሽት እንደሚኖሩትም ታውቋል፡፡