የውጭ ተፅእኖዎችን ለመቋቋም የውስጥ ሠላምና አንድነትን ማጠናከር ይገባል - አስተያየት ሰጪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ተፅእኖዎችን ለመቋቋም የውስጥ ሠላምና አንድነትን ማጠናከር ይገባል - አስተያየት ሰጪዎች
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2013 ከውጭ የሚደርሱ ተፅእኖዎችን ለመቋቋም ኢትዮጵያዊያን የውስጥ ሠላምና አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ ቪዛን ጨምሮ ፣ ወታደራዊና ከደህንነት ጋር የተያያዙ ድጋፎች ላይ ማዕቀብ መጣሏን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ትናንት መግለጻቸው ይታወቃል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በምላሹ አሜሪካ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን ከቀጠለች ከአገሪቷ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጤን እንደሚገደድ አስታውቋል።
ኢዜአ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ያነጋገራቸው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚደርሱ የውጭ ተጽእኖዎች ለመቋቋም የውስጥ ሠላምና አንድነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድም ዜጎች የውስጥ አንድነታቸውን በማጠናከር አገሪቱ የሚገጥሟትን ችግሮች በጋራ መመከት አለባቸው።
ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር ከተቻለ የአገሪቷን የተፈጥሮ ሃብቶች ጥቅም ላይ በማዋል ኢኮኖሚዋን ለመደገፍም አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።
ከስተያየት ሰጪዎች መካከል ሙሃባ ሻፊ ሕዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ ከቀጠለ ምንም አይነት ጫና ቢመጣ መቋቋም ይቻላል ብላለች።
"በአሜሪካ አይደለም የምንኖረው። እኛ ከተባበርን ኢትዮጵያን ቀርቶ ሌላም መገንባት እንችላለን። በቂ ንብረት በቂ ሃብት አለን፤ የተፈጥሮ ሃብት አላት፤ ይህንን ጥሩ አድርጎ የሚያስፈጽም ሰው ካለ አሜሪካ የምትጎዳን ነገር አይኖርም። የሚለው ደግሞ አቶ በላቸው ዓለማየሁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ማዕቀብ የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ግንኙነት ያላገናዘበ፣ ለአሜሪካ ሕዝብና መንግሥት የማይጠቅምና ቀጣናውን ችግር ውስጥ የሚከት መሆኑን በዛሬ መግለጫው አስታውቋል።
ማዕቀቡ ለ120 ዓመት የዘለቀውን የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት እንደሚያሻክርም አመልክቷል።