የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ነጻነት በምንም የማይለወጥ የሕልውና ጉዳይ ነው...የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ነጻነት በምንም የማይለወጥ የሕልውና ጉዳይ ነው...የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ነጻነት የማይታለፍ ቀይ መስመር፤ በገንዘብም የማይለወጥ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትግራይ ያለውን እውነታ መቀበል ያልፈለገው ከመረጃ እጥረት ሳይሆን ጉዳዩን ከጥቅም ጋር ስላያያዘው እንደሆነም ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በአበይት የዲፕሎማሲ ክንውኖች ላይ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አሜሪካ በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ቀውስ ተጠያቂ እና ተባባሪ የሆኑ እንዲሁም ቀውሱን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት አስተጓጉለዋል በሚል ትናንት በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለስልጣናት ላይ የቪዛ ገደብ የጣለች ሲሆን ለኢትዮጵያ መንግስት በምትሰጠው የምጣኔ ሀብትና የደህንነት ድጋፍ ላይም ዕቀባ ጥላለች።
አሜሪካ የጣለቻቸው ገደቦች ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ያላገናዘበና ለአሜሪካ መንግስትና ሕዝብ ጭምር የማይጠቅም መሆኑን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
አገራቱ በቀጣናው ሠላምና ደህንነት በማስጠበቅ እንዲሁም ሽብርተኝነት ለመከላከል በትብብር የሚያከናውኑት ሥራ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
የቪዛ ገደቡና ሌሎች ተዛማጅ እርምጃዎች በኢትዮጵያ መንግስት ተቀባይነት እንደሌላቸውና አሜሪካ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያበቃ ምክንያት እንደሌላት አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያለውን ጉዳይ 'ማጋጋል' አትፈልግም፤ የሁለትዮሽ ግንኙቱ እንዲበላሽ አትሻም፤ አሜሪካ ውሳኔዋን ዳግም ታጤነዋለች ብለን ተስፋ እናደርጋለን ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ነጻነት የማይታለፍ ቀይ መስመር፤ በገንዘብም የማይቀየር የሕልውና ጉዳይ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ዲና ይህንን ሁሉም ሊያውቀው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትግራይ ክልል ያሉ እውነታዎችን እየካደ መሆኑን፤ ይህም ያለውን ሁኔታ ካለማወቅ የመነጨ ሳይሆን ጉዳዩን ከራስ ጥቅም ጋር በመያያዙ እንደሆነ አክለዋል።
በትግራይ ክልል ከሠብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነትና አቅርቦት እንዲሁም ከሠብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ ይነሱ የነበሩ ጉዳዮች ምላሽ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።
አምባሳደር ዲና በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ባለፈው ሣምንት 1 ሺህ 316 ዜጎች ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ አገራቸው መመለሳቸውንም አያይዘው ገልጸዋል።
በተጨማሪም በአውሮፓ የሚገኝ "ዲፌንድ ኢትዮጵያ" የተሰኘ ግብረ ሃይል አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት በመቃወም የበይነ መረብ ተቃውሞ ማድረጉን አስታውሰዋል።