አገራት ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥሩትን ጫና በተባበረ ክንድ መመከት ይገባል-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
አገራት ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥሩትን ጫና በተባበረ ክንድ መመከት ይገባል-ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17/2013 ( ኢዜአ) የተለያዩ አገራት ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥሩትን ጫና በተባበረ ክንድ መመከት ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል የሚደረገውን የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደሚቃወሙም አመልክተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የሥራ ኃላፊዎች ላይ የጣለው የቪዛ ማዕቀብ አድሎዓዊ ውሳኔ መሆኑን ነው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች የገለጹት።
የአሜሪካ አስተዳደር በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራዎች መደገፍና ማበረታታት ሲገባው ያልተገቡ ውሳኔዎች በማሳለፍ ጫና ለመፍጠር መሞከሩ ተገቢ አይደለም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ዜጎች የጋራ ትብብር እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ዜጎች በጉጉት እየጠበቁት መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
ይሁንና የግድቡ ግንባታ እንዳይጠናቀቅ፣ ህዝቡ ከጨለማ እንዳይወጣና አገርም ተጠቃሚ እንዳትሆን የሚፈልጉ ኃይሎች አገሪቱ ላይ ጫና ለማሳደር እየሞከሩ መሆኑን ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ መጻዒ ሃያልነት የሚያሰጋቸው አገሮች የኢትዮጵያን የልማት ሥራዎች በማደናቀፍ የሚፈጥሩትን ጫና የኢትዮጵያ ህዝብ በተባበረ ክንድ መመከት እንዳለበትም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
ህዝቡ ከሚያለያይ ይልቅ አንድ የሚያደርገውን ጉዳይ በማጉላት አገራዊ አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበት በመግለጽ።
አቶ አብዱራህማን ፈለቀ " የኢትዮጵያ ህዝብ ቀድሞም ተሞክሯል፤ ታይቷል፤ ይሄ አይነት ተጽዕኖ አይበግረንም፤ ከተባበርን ምንም ነገር አይበግረንም ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ቴድሮስ ዳይኖ በበኩላቸው "ኢትዮጵያውያን አንድ ላይ በመሆን የጋራ ጠላታችንን በጋራ የምንመክትበት አንድ ላይ የምንቆምበት በጋራ ቆመን ይሄንን ድል የምናደርግበት ወቅት ነው'' ብለዋል ።
ሰብለወርቅ ደሴ የቀደሙ አባቶች ያለ ብሄር፣ዘርና ሀይማኖት ልዩነት ሁሉም ለአገራቸው በጋራ የወጡት አንድ ላይ መሆኑን ይናገራሉ።
''ትልቁ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ልብ ከሆነ ግድቡ ይገደባል ማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት አያስፈልገንም'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሰብለ ታዬ ናቸው።
ወጣት ሚኪያስ መሰለ በበኩሉ "የአገር ሉዓላዊነትን ከፍ ለማድረግ ወጣቱ በአንድነት፣ በመተሳሰብ፣ በመደራጀት መነሳት አለብን'' ሲል ተናግሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትላንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የአሜሪካ አስተዳደር በመንግስት የስራ ሃላፊዎች ላይ ያደረገውን የቪዛ ክልከላ ጨምሮ መሰል እርምጃዎች የአገራቱን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ሊጎዳው ይችላል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የምታደርገው ሙከራ ተገቢነት የሌለው ብቻ ሳይሆን ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ሚኒስቴሩ አጽንኦት መስጠቱ የሚታወስ ነው።
አገሪቱ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን የምትቀጥል ከሆነ መንግሥት ከአገሪቱ ጋር ያለውን ግንኙነት መለስ ብሎ ለማጤን እንደሚገደድ ማስታወቁም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ አስተዳደር ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ ገንቢ የሆነ ግንኙነት እያደረገ ባለበት ጊዜ ውሳኔው መሰጠቱን ያስታወሰው መግለጫው፤ ለምርጫ ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት መሆኑ ደግሞ የተሳሳተ መልዕክት የሚያስተላለፍ ነው ብሎታል።