ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተናዎች ከግምት በማስገባት ለምርጫው ሰላማዊነት እየሰሩ መሆኑን የተለያዩ ፓርቲዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተናዎች ከግምት በማስገባት ለምርጫው ሰላማዊነት እየሰሩ መሆኑን የተለያዩ ፓርቲዎች ገለጹ
አዲስ አበባ ግንቦት 17/2013/ ኢዜአ/ ኢትዮጵያ ከውጭና ከውስጥ ያጋጠማትን ፈተና ከግምት በማስገባትና አገርን በማስቀደም ለምርጫው ሰላማዊነት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ ለ2013 ዓ.ም ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የቅድመ ምርጫ፣ ምርጫና ድህረ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ አውጥታ እየሰራች ትገኛለች።
ቦርዱ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በማድረግ የህዝብ ድምጽ ለማግኘት ችግሮችን ተቋቁመው እየሰሩ እንደሚገኙ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተፎካካሪ ፓርቲ ኃላፊዎች ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዜጎቿ ድምጽ ቀጣይ እጣ-ፈንታዋን በሚወስነው በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ውስጥ ብትሆንም ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች እየፈተኗት መሆኑን አንስተዋል።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ቅድመ ምርጫው በበርካታ ችግሮች ውስጥ እየሄደ ቢሆንም የነገዋን ኢትዮጵያ በማስቀደም እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን አስከብራ እንድትቀጥል ምርጫው እስከመጨረሻው ፍትሃዊ፣ ገለልተኛ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንደሚካሄድ እምነታቸውን ገልጸው ለዚህም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የእናት ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰይፈሥላሴ አያሌው በበኩላቸው፤ መንግሥት ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ቀደም ሲል ከተካሄዱት በተሻለ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ አደርጋለሁ ቢልም በሂደቱ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ስጋት ፈጥረውባቸዋል።
ይሁን እንጂ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለማለፍ ኢትዮጵያ ያለችበትን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት በአንድነት መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸው የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል።
በታችኛው የመንግሥት መዋቅር የሚገኙ ኃላፊዎች አገርን ከማስቀደም ይልቅ ከምርጫው በኋላ የግል እጣ- ፈንታቸው ላይ የማተኮር አዝማሚያ እንደሚታይ ገልጸው ይህም መታረም እንዳለበት መክረዋል።
እስካሁን በነበረው የስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ሂደት በፓርቲዎችና በምርጫ አስፈጻሚው በኩል የነበሩ ችግሮችን በመዘርዘር በቀጣይ በትብብር መሥራት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር ናቸው።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ በሂደቱ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሄደበት ርቀት ሊያስመሰግነው ቢገባም በቂ አይደለም ብለዋል።
በዘንድሮው አጠቃላይ ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መገናኛ ብዙኃንን፣ የአደባባይ ትዕይንቶችንና ሌሎች መረጃ ማስተላለፊያ መንገዶችን በመጠቀም ለመራጩ ህዝብ ያላቸውን አማራጭ ሐሳብ እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች የድምጽ መስጫውን ቀን ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓም ለማካሄድ ቀን ቆርጦ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።