ቀጥታ፡

በግንባታ ሂደት ላይ ከሚገኙ የኃይል ማከፋፈያና ማሰራጫ ጣቢያዎች አምስቱ የሙከራ ስርጭት ጀመሩ

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2013/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እያስገነባቸው ከሚገኙት የኃይል ማከፋፈያና ማሰራጫ ጣቢያዎች አምስቱ የሙከራ ስርጭት መጀመራቸውን አስታወቀ።

ተቋሙ ከ132 ኪሎቮልት እስከ 500 ኪሎቮልት ድረስ ያሉ ከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ መሥመሮችን ይዘረጋል።

የኃይል ማከፋፈያና ማመንጫ ጣቢያዎችን ገንብቶም ያስተዳድራል።

ከአገሪቷ ግድቦች የመነጨውን ኃይል ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ከኃይል ማመንጫ እስከ ማከፋፈያ ድረስ ያሉ ተግባራትንም ያከናውናል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት ተቋሙ 16 የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያና ማሰራጫ ጣቢያዎችን በመገንባት ላይ ነው።

ከነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልአምስቱን ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ የሙከራና የፍተሻ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

ፕሮጀክቶቹ ለአገልግሎት የሚበቁት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የገናሌ ዳዋ ሶስተኛ-ይርጋለም-ወላይታ ሶዶ፣ የባህርዳር-ወልድያ-ኮምቦልቻ፣ የአቃቂ-ደብረ ዘይት-ሞጆ ጊንጪና የአዲስ አበባ-ጊቤ ሁለት ሁለተኛ ሰርኪዩት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

ከነዚህም የአዲስ አበባ-ጊቤ ሁለት ሁለተኛ ሰርኪዩት ለአገልግሎት መብቃቱን አቶ ሞገስ ተናግረዋል።

ከወሰን ማስከበርና ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙ ያነሱት ዳይሬክተሩ በአንዳንድ አካባቢዎች የወሰን ይገባኛል ሳይኖር ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ የካሳ ጥያቄዎች እንደሚመጡ ጠቁመዋል።

ይህም ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ ከማድረጉ ባሻገር ወጪያቸውንም እያናረው ይገኛል ብለዋል።

ተቋሙ ተጣርቶ የመጣለትን አረጋግጦ የካሳ ክፍያ እንደሚፈጽም የገለጹት አቶ ሞገስ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ችግሩን ለመፍታት ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

በሶዶ ቡኢ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ጣቢያ ባለሙያ አቶ አክሊሉ ዌና በበኩላቸው በቡኢ ከተማ እየተገነባ ያለው  የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የአካባቢውን ከተሞች የኃይል ችግር እንደሚቀርፈው ገልጸዋል።

ከጣቢያው የሚወጣው ኃይል ቡኢ፣ ተሬና ኬላ ከተሞችን በዋነኝነት ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ውሃን ጨምሮ ከተለያዩ አማራጮች ኤሌክትሪክ በማመንጨት ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም