ባለሃብቱ በጥቃቅን ጉዳዮች እንዳይጉላላ አመራሩ በቁርጠኝነት መደገፍ አለበት - አቶ ገዱ አንዳርጋቸው - ኢዜአ አማርኛ
ባለሃብቱ በጥቃቅን ጉዳዮች እንዳይጉላላ አመራሩ በቁርጠኝነት መደገፍ አለበት - አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
ደሴ፤ ግንቦት 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ባለሃብቶች በጥቃቅን ጉዳዮች ሳይጉላሉ የተሻለ ልማት እንዲያከናውኑ አመራሩ በቁርጠኝነት መደገፍ እንዳለበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።
በደሴ ከተማ በተካሄደው የኢንቨስትሙንት ፎረም ላይ የተገኙት አቶ ገዱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለችና ጥሬ ሃብት ቢኖራትም በአግባቡ ለምቶ መጠቀም አልተቻለም፡፡
በተለይም ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ሀብቱን ጥቅም ላይ ለማዋል የመሬት አቅርቦት፣ ካሳ ክፍያ፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ መሰረተ ልማት አቅርቦት፣ የውጭ ምንዛሬና ሌሎችም ጉድለቶች ፈተና መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀላሉ መፈታት በሚችሉ ጥቃቅን ጉዳዮች ባለሃብቱ ሲጉላላ መመለክት አሳፋሪ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞንና በወረዳ ደረጃ መስተካከል የሚችሉ ችግሮችን ወደ ክልልና ፌዴራል በመግፋት ባለሃብቱን ማጉላላትና ህብረተሰቡን ጥቅም ማሳጣት ተገቢ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።
ለመፍትሄውም አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ባለሃብቱን በአግባቡ በመያዝ የስራ እድል መፍጠርና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት መሞከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከዞንና ወረዳ አቅም በላይ የሆኑ ችግሮችን የክልልና ፌደራል መንግስት በፍጥነት ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
በየአካባቢው የተገነቡ ፋብሪካዎችንም ከግብርና ምርቶች ጋር ተመጋጋቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ለባለሃብቶች መሬት ሲሰጥ ያልተቆራረጠ ግብዓት በቀላሉ የሚያገኙበት ቦታ ላይ መሆን እንዳለበትም አመልክተዋል።
መንግስት ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለሃብቱም መሬት ከማጠርና ምክንያት ከማብዛት ተቆጥቦ በሚችለው አቅም ለማልማት በቅንጅት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
የፌዴራል የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ከበደ ይማም በበኩላቸው አካባቢን የማይበክሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲስፋፉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለኢንቨስትመንቱ እድገት ወሳኝ የሆነውን ሰላም ተቀናጅቶ በማስጠበቅ የባለሃብቶችን ቀልብ ለመሳብ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ የዘርፉ ችግሮች ምንጭ ተቀናጅቶ ያለመስራት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ ዞኑ የመሰረተ ልማት፣ የመሬት አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን እየፈታ በመሆኑ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ቅድሚያ የሚሰጣቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች መለየታቸውንም ገልጸዋል።
ደረቅ ወደብ፣ ባቡር ጣቢያ፣ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ኢንዱስትሪ ፓርክና ሌሎችም ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸው አካባቢው ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርገውም አብራርተዋል፡፡
በደሴ ከተማ ትናንት በተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረምም የፌዴራል፣ ክልልና ዞን አመራሮች እንዲሁም ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።