የኢንዶኔዥያ ባለሀብቶች ከኢትዮጵያዊያን አቻዎቻቸው ጋር ተባብረው እንዲሰሩ ድጋፍ እየተደረገ ነው...አምባሳደር አልቡሽራ ባስ ኑር - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዶኔዥያ ባለሀብቶች ከኢትዮጵያዊያን አቻዎቻቸው ጋር ተባብረው እንዲሰሩ ድጋፍ እየተደረገ ነው...አምባሳደር አልቡሽራ ባስ ኑር
ደሴ፤ ግንቦት 17/2013 (ኢዜአ) የኢንዶነዥያ ባለሀብቶች ከኢትዮጵያዊያን አቻዎቻቸው ጋር በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተባብረው እንዲሰሩ ለማገዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አልቡሽራ ባስ ኑር ገለጹ፡፡
አምባሳደሩ በደሴ ከተማ በተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ ሀገራት ናቸው፡፡
ባለሃብቶች በሁለቱም ሀገራት ከተሞች የልምድ ልውውጥ እንዲያደረጉ መደረጉን ጠቁመው፤ ጥሩ መነቃቃት በመታየቱ እንዲሰፉ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተሰማርተው የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና የስራ እድል በመፍጠር የወዳጅነት ግዴታቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል።
ከአስመጭና ላኪ ባለሃብቶችም ጋር በመቀናጀት የኢንዶኔዥያ ምርቶችን ወደ ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ምርቶችን ደግሞ ወደ ኢንዶኔዥያ በቀላሉ ተደራሽ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አሰረድተዋል።
ግንኙነቱን በማጠናከር የሀገራቸው ባላሀብቶች ከኢትዮጵያዊያን አቻዎቻቸው ጋር በቅንጅትና ትብብር እንዲሰሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ የበለጠ ስራውን ለማቀላጠፍ ከአቻ አስተዳደሮችና ከተሞች ጋርም ቁርኝት እንዲፈጥሩ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
''በወሎ ያለውን ምቹ ሁኔታም ለመጠቀም ከክልልና ፌደራል መንግስት ጋር እየሰራን ነው'' ያሉት አምባሳደሩ በተደጋጋሚ አካባቢውን መጉብኘታቸውንና የሚሰማሩበትን የስራ ዘርፍም እያጤኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌሎች ባለሀብቶችም በግብርናና በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ለመሰማራ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው ፤"እሴት በመጨመር አርሶ አደሩን ጭምር ተጠቃሚ ማድረግና ለወጣቱ የስራ እድል መፍጠርም ዓላማችን ነው" ብለዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰይድ ኑሩ በበኩላቸው፤ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ተጠናክሮ በክልሉ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ባለሃብቶች እንዲሰማሩ ከፌደራል መንግስት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ከአቻ ከተሞችና ባለሃብቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠርም የልምድ ልውውጥና የቴክኖሎጅ ሽግግር እንዲያደርጉ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ከውጭ የሚገባውን 70 በመቶ የግንባታ ግብዓትም በሀገር ውስጥ እንዲተካ ባለሃብቶች መስራት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ መንግስት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ከኢንዶኔዥያ ባለሃብቶች ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በአስመጭና ላኪ ስራ የተሰማሩት ኢትዮጵያዊው ባለሃብት አቶ አህመድ ሐሰን ናቸው፡፡
የግብርና ምርቶችን ጨምሮ ሌሎችን ወደ ውጭ ሃገራት በመላክ የፋብሪካና ሌሎች ውጤቶችንም ወደ ሀገር ውስጥ በማስመጣት የሁለቱን ግንኙነት ለማጠናክር የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከባለብቶች ጋር የልምድና የቴክኖሎጅ ለውውጥ ማድረጋቸው የበለጠ እንዲሰሩ ያነሳሳቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ምቹ ሁኔታ ለፈጠሩላቸው የሁለቱ ሀገራት አምባሳደሮችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አምባሳደር አልቡሽራ ባስ ኑር ባለፈው ዓመት በወሎ ባደረጉት የሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ከባለሃብቶች ጋር እንደተወያዩም ተገልጿል፡፡