ቀጥታ፡

በሰሜን ካሮላይና የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከ41 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረጉ

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2013 ዓ.ም በአሜሪካ ሰሜን ካሮላይና ግዛት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ41 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

የሰሜን ካሮላይና የሕዳሴ ግድብ ድጋፍ አሰባሳቢ ግብረ ሃይል ተወካዮች ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመገኘት የገንዘብ ድጋፉን አስረክበዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ድጋፍ ላደረጉ ዜጎች ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ከግድቡ ድጋፍ በተጨማሪ በሰሜን ካሮላይና ግዛት የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ያልተገባ ጫና ለማክሸፍ የተደራጀ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በማቋቋም እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የግብረ ሃይሉ ተወካዮች በበኩላቸው ለሕዳሴው ግድብና ሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል ቃል መግባታቸው ተገልጿል።

በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ አክሎ እንደገለጸው በቅርቡ በሰሜን ካሮላይና ግዛት የሚኖሩ የዳያስፖራ ወገኖች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበት ውይይት እንዲሁም የቢዝነስና የድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረክ ለማዘጋጀት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ዳያስፖራው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም