ኦማር ሀሰን አልበሺር የካቢኔ ሹም ሽር አካሄዱ

67
ግንቦት 7/2010 ፕሬዚዳንቱ  በካቢኔ ሹም ሽራቸው ሰባት አዳዲስ ሚኒስትሮችን፣ ስምንት የግዛት አስተዳዳሪዎችን እና አምስት የግዛት የስራ ሃላፊዎችን ሾመዋል። በዚህም መሰረት በቅርቡ ከሃላፊነት በተነሱት ኢብራሂም ጋንዱር ምትክ አል ዲየርዲሪ አል ዲኬሪን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርገው ሹመዋል። ፕሬዚዳንቱ የነዳጅ፣ የሀገር ውስጥ፣ የግብርና፣ የወጣቶችና ስፖርት እንዲሁም የፍትህ ሚኒስትሮችን በአዲስ ተክተዋል። አዲስ ከተሾሙት መካከል ኢብራሂም ሃሚድ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር እንዲሁም አዝሃሪ አብደላ የነዳጅ  ሚኒስትር ሆነዋል። ፕሬዝዳንቱ የካቢኔ ለውጥ ያደረጉት በሀገሪቱ ያለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መባባሱን ተከትሎ ነው ተብሏል። በሱዳን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ መታየቱን ተከትሎ ሀገሪቱ ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተዳርጋለች። ይህን ቀውስ ለማረጋጋትም ማዕከላዊ ባንኩ  ከጥር ወር ጀምሮ የሀገሪቱን ገንዘብ የምንዛሬ አቅም  ሁለት ጊዜ ማዳከሙ ይታወቃል። በሀገሪቱ የዋጋ ግሽበቱ 56 በመቶ  ማስመዝገቡ፣ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ማጋጠሙ እንዲሁም የምግብ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ህዝቡን ለቅሬታ እየዳረገ መሆኑንም ረጃዎች ያሳያሉ። ምንጭ፦ ሲ ጂ ቲ ኤን
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም