ጥራት ያለው የቡና ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚያስችል የማክሮ ሎት የግብይት አሰራር ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ጥራት ያለው የቡና ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚያስችል የማክሮ ሎት የግብይት አሰራር ይፋ ሆነ
ግንቦት 16/2013 (ኢዜአ) ከኢትዮጵያ ጥራት ያለው የቡና ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚያስችል የማክሮ ሎት የግብይት አሰራር መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ይፋ አደረገ።
አዲሱ የግብይት ስርአት ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ተግበራዊ መደረግ ይጀምራል ተብሏል።
ለባለ ልዩ ጣዕም ቡና በልዩ ሁኔታ የማይክሮ ሎት ግብይት ሥርዓት መዘርጋቱን በማስመለከት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ በሰጡት መግለጫ ጥራት ያለው የቡና ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ለባለ ልዩ ጣዕም ቡና በልዩ ሁኔታ የማክሮ ሎት የግብይት አሰራር መዘጋጀቱን ይፋ አድርገዋል።
የማይክሮ ሎት ግብይት ሥርዓት በላብራቶር ተረጋግጦ ከ85 በመቶ በላይ ጥራት ያለውና የምርት ዱካው የተረጋገጠ ቡና የሚገበያይበት ሥርዓት እንደሆነ ተገልፇል።
የግብይት ሥርዓቱ የጥራት ደረጃ ያለው ቡና ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል፣ የአርሶ አደሩን ገቢ ከፍ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።
ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ጠቀሜታ እንዳለውም አብራርተዋል።
የማይክሮ ሎት ግብይት ሥርዓት በከፍተኛ ዋጋ የሚከናወን ሲሆን በአስተማማኝ የገበያ መረጃ ሥርዓት ሁሉም የግብይት ተዋናንያን ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑም ተመልክቷል።
ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ የሚጀመረው የማይክሮ ሎት ግብይት ሥርዓት በብሄራዊ ደረጃ አሸናፊ የሆኑ አርሶ አደሮችን ቡና በማገበያየት እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
የቡና ምርቱ ለውድድር ተብልው በተዘጋጁ በአዲስ አበባ፣ በጅማና ሀዋሳ ባሉ ልዩ መጋዝኖች የሚገኝ ሲሆን የጥራት ደረጃው በውድድር ተፈትሾ ውጤት እንደተሰጠው ጠቁመዋል።
የአትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ፤ የግብይት ሥርዓቱ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አነሳሽነት የተጀመረ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
አሰራሩን መዘርጋት የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑ የቡና ምርቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ እንዲንሆን እና በዋጋ የመደራደር አቅም የሚጨምር መሆኑንም ገልጸዋል።
አዲሱ የግብይት ሥርዓት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ እና ሌሌች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሰራ እንደሆነ ዶክተር አዱኛ ገልፀዋል።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር እና ፊድ ዘ ፊውቸር ኢትዮጵያ ቫሊዩ ቼይን አክቲቪቲ እና አሊያንስ ፎር ኤክሰለንስ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገውን የ2013 የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ኢትዮጵያ አሽናፊዎች በጋራ ይፋ አድርገዋል።
በውድድሩም 87 ነጥብ በማምጣት 30 የቡና የምርት አይነቶች አሸናፊ ሲሆኑ አምስት የቡና ምርት አይነቶች ደግሞ ከ90 በመቶ በላይ በማምጣት የፕሬዚደንሻል አዋርድ እውቅና እንዳገኙ ተገልፇል።
የውድድሩ አሸመናፊ የሆነው የቡና ምረት ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም በአሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ድረ ገፅ ላይ በሚደረግ 24 ሰዓት የቀጥታ የኢንተርኔት ግብይት በጨረታ ለሽያጭ ይቀርባል ተብሏል።
የተገኙ ውጤቶችም በዓለም አቀፍ ስፔሻሊት የቡና ገበያ ከፍ ያለ እርካታ መፍጠር እንደቻሉ ተገልጿል።