የኢትዮጵያን የዓባይ ውሃ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥናትን ያማከለ ሥራ ያስፈልጋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የዓባይ ውሃ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥናትን ያማከለ ሥራ ያስፈልጋል ተባለ
ግንቦት 16 / 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በዓባይ ውሃ ጉዳይ ያላትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥናትን ማዕከል ያደረገ ያልተቋረጠ ሥራ መስራት እንደሚያስፈልጋት ምሁራን ገለጹ።
ምሁራኑ ይህን የገለጹት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በየዓመቱ በሚካሄደው የምርምር ሳምንት መክፈቻ ላይ ባቀረቡት ፅሁፍ ነው።
"ምርምር ለሠላምና ለአገር ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ መካሄድ የጀመረው የምርምር ሳምንት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ በተገኙበት ተከፍቷል።
በመርሃ ግብሩ የአራት ቀናት ቆይታ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሽግግር ከጂኦ ፖለቲካል ዕይታ፣ በሽግግር ወቅት ያለ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ኮቪድ-19 እና የኢትዮጵያ ሽግግር እንዲሁም የኢትዮጵያ ሽግግርና ምርጫ በሚሉ ጉዳዮች ጥናታዊ ፅሁፎች ይቀርባሉ።
ከጥናታዊ ፅሁፎቹ መካከል የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሽግግር ጂኦፖለቲካዊ ዕይታ የተመለከተው ፅሁፍ በምሁራን ከተለያየ አውድ አንጻር ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በፅሁፉ በኢትዮጵያ ስላለው የሠላም ሁኔታ፣ የሕዳሴ ግድብና ተያያዥ ዓለምአቀፋዊ እና አገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ፖለቲካውን የተመለከቱ ይዘቶች ጎልተው ወጥተዋል።
የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ የውይይት መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ ግድቡ ለኢትዮጵያዊያን የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የህልውና፣ የዓለም አቀፍ ተሰሚነትና የብሔራዊ ኩራት መገለጫ መሆኑን አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ የግድቡ ግንባታ ከመጀመሩ በፊትም ይሁን ከተጀመረ በኋላ የግድቡንና የኢትዮጵያን የዓባይ ውሃ ተጠቃሚነት በተመለከተ የሚደረጉ ሁለንተናዊ ተሳትፎዎች አናሳ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ከዚህ አኳያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለአብነት የጠቀሱት ዶክተር ሳሙኤል፣ "በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮች ላይ ምሁራንን ከማሳተፍ ባለፈ እንደ አንጋፋነቱ አልሰራም" ብለዋል።
ለዚህም የምርምር ስራዎችን ከመስራት፣ የተለያዩ አጀንዳዎችን ከማዘጋጀትና ሃገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ከመፍጠር አአኳያ ሚናው ዝቅተኛ መሆኑን በጽሁፋቸው ጠቁመዋል።
የሕዳሴው ግድብና የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነት በአንድ ጊዜ የሚፈታ ባለመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ይህን አውቀው ተቋማዊና በጥናት ላይ የተመሰረተ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
በመሆኑም ከመንግስት በኩል ምሁራንን የማሳተፍና የሕዳሴ ግድብና የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነትን በተመለከተ መረጃ የሚያደራጅና የሚሰበስብ ጠንካራ ተቋም መፍጠር እንደሚገባ ተመላክቷል።
በዚህም ሁሉም ዜጎች ስለ ዓባይና ስለ አገራቸው በአግባቡና በጥልቀት አውቀው ያገባኛል እንዲሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተነስቷል።
የኢትዮጵያን ሽግግር ከጂኦ ፖለቲካዊ ዕይታ አንፃር አስመልክተው ፅሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ዮናስ አሽኔ በበኩላቸው ዓለም አቀፉ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ በተለያየ መንገድ ያለውን ጫና አብራርተዋል።
በተለይ የአገራት ግላዊነት ማደግ፣ የዴሞክራሲ መንሸራተት፣ የሃያላን አገራት ሽኩቻ፣ የባህርና የየብስ ቦታዎች ቅርምት በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በቀጥታ ጫና እንዳለው ነው ያስረዱት።
"በአሁኑ ወቅት ዓለም ወደ አዲስ ታሪክ እየገባችና ሌላ አዲስ ዴሞክራሲን የሚተካ ስርዓት እየፈለገች ያለችበት ሁኔታ የመጣ ይመስላል" ያሉት ዶክተር ዮናስ እነዚህን ጉዳዮች በአንክሮ ማየት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በአገራዊ ሠላም ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረጉት ሌላው ምሁር ዶክተር ዮናስ አዳዬ ደግሞ ሠላም ዓለም አቀፋዊና ተያያዥ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
አንዱ ሠላሙን አጥቶ ሌላው ሠላም ለመሆን እንደማይችል የጠቀሱት ዶክተር ዮናስ፣ "በተለይ ለኢትዮጵያ ተቋማዊና ቀጣይነት ባለው መንገድ ትውልድን መቅረፅና ማስተማር ያስፈልጋል" ብለዋል።
ከሕገ መንግስት ማሻሻል ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚታዩትን የጎሳና የመከፋፈል ፖለቲካ ማስተካከል እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።