ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቅንነት ስራቸውን ለሚሰሩ ጋዜጠኞችን ለማስተናገድ ዝግጁ ናት... የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን

ግንቦት 16 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በቅንነት ስራቸውን ለሚሰሩ ጋዜጠኞችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።

“ኢትዮጵያ ሃሳብን በነጻነት መግለጽንና የፕሬስ ነጻነትን በተመለከተ ያላትን ጽኑ አቋም ደጋግማ አስታውቃለች” ሲል ባለስልጣኑ መግለጫ አውጥቷል።

ሃሳብን በነጻነት መግለጽንና የፕሬስ ነጻነትን ጥበቃ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት በክብር የተቀመጠ እሴት መሆኑን ገልጿል።

ለእነዚህ እሴቶች መጠበቅ የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ ቁርጠኝነቱ በተግባር የተተረጎመ ስለመሆኑንም አመልክቷል።ለአብነትም ጋዜጠኞችና ፖለቲካ ከእስር መፈታታቸውን አንስቷል።

ይህ ብቻ ሳይሆን በርካታ የለውጥ ተግባራት ባለፉት ሶስት አመታት ተከናውነው የሃሳብ ነጻነት ምህዳር እንዲሰፋ መደረጉን ጠቅሷል።ቀደም ባሉት አመታት ሃሳብን በመግለጽና በፕሬስ ነጻነት ላይ ገደብ የሚጥሉ እንቅፋቶች እንዲነሱ ተደርጎ ለአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች መረጃ የሚያገኙበት ምቹ መደላደል መፈጠሩን ገልጿል።

በአገሪቱ ውስጥ እንዲሰሩ ፈቃድ የተሰጣቸው 35 የውጭ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት 129 ቋሚ ነዋሪነት ፈቃድ ያላቸው ዘጋቢዎች እንዳሏቸው አመልክቷል።

ከዚህ ባለፈም በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ ለ82 የውጭ ጋዜጠኞች ጊዜያዊ ፈቃድ ተሰጥቶ ያለውን ሁኔታ መዘገብ የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸቱን አመላክቷል።

“እኛ ጠብቀን የነበረው የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርን ከግምት ያስገባ በሙያ ላይ የተመሰረተ ዘገባ ነበር” ያለው መግለጫው፤ በጋዜጠኞቹ ጥንቃቄ የሚያሻቸው ጉዳዮች ላይ ተገቢው ጥንቃቄ ይደረግባቸዋል የሚል ግምት እንደነበረው አውስቷል።

በየትኛውም ዓለም እንደሚደረገው ወታደራዊ ዘመቻ በሚካሄድበት አካባቢ ገደብ እንደሚጣል ያነሳው መግለጫው፤ ፈቃድ የተሰጣቸው ዘጋቢዎችም ይህንን እውነታ አክብረውና ጠብቀው ይሰራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።

ነገር ግን የህግ ጥሰት ሲያጋጥም በየትኛውም የዓለም ክፍል እንደሚደረገው ባለስልጣኑ ህግን የማስከበር ሃላፊነቱን የመወጣት ግዴታ እንዳለበት ገልጿል።

በዚህም መሰረት የዓለም ዓቀፍ ተሞክሮን በመከተል በትብብር ለመስራት እንደሚሞክር አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም