ቀጥታ፡

የአሜሪካ መንግስት ውሳኔ ኢትዮጵያ ከአሜሪካን ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት መልሳ እንድትገመግም ያስገድዳታል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ግንቦት 16 / 2013 (ኢዜአ) በአሜሪካ መንግስት የተላለፉ የቪዛ ገደቦችና መሰል ውሳኔዎች የአገራቱን የተጠናከረ ወዳጅንት ከመሸርሸሩ ባለፈ ኢትዮጵያ ከአሜሪካን ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት መልሳ እንድትገመግም እንደሚያስገድዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በአሜሪካ መንግስት የተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከአሜሪካ ጋር በአወንታዊ እና ገንቢ ግንኙነት የሀሉትዮሽ ትስስሩን ባጠናከረበት ወቅት እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች ተገቢነት የሌላቸው መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ አሜሪካ ያደረገችው የቪዛ ክልከላም የሁለቱን አገሮች የረጅም ጊዜ የተጠናከረ ወዳጅነት የሚሸረሽር ተግባር መሆኑን አስገንዝቧል።

የሁለቱን አገሮች ጠንካራ ግንኙነት በሚያሳይ መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በቅርቡ የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክትኛ ተደርገው ከመጡት ጄፍሪ ፌልትማን ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ምክክር ማካሄዳቸውን አስታውሷል።

በተጨማሪም አዲስ ፖለቲካዊ ሽግግር ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀውን ብሔራዊ ምርጫ ለማካሄድ ኢትዮጵያ እየተዘጋጀች ባለበትና የአሜሪካን ድጋፍና መረዳትን በምትጠብቅበት በዚህ ወቅት በምርጫው ላይ መጥፎ ጥላ ሊያጠላ የሚችል ውሳኔ መታሰብ አልነበረበትም ብሏል።

አሜሪካ ያደረገችው የቪዛ ክልከላም የአገሮቹን የረጅም ጊዜ የተጠናከረ ወዳጅንት የሚሸረሽር ተግባር መሆኑን አመልክቷል።

መንግስት የኢትዮጵያን ብልጽግናን ለማሳካት ከመላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር ብሔራዊ ምክክርን እያደረገ እንደሚገኝ የገለጸው መግለጫው፤ ይህም ያለማንም የውጭ አማካሪ አመልካችነት እየተተገበረ እንደሚገኝ ነው ያስታወቀው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በአሸባሪነት ከተፈረጀው ህወሃት ጋር በምንም አይነት ሁኔታ እንደማይደራደር መታወቅ ይኖርበታል፣ የሽብር ቡድኑን እንደገና ለማነቃቃት የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ሙከራ ውጤታማ የማይሆንና መንግስት የማይታገሰው ጉዳይም ነው ብሏል።

ከዚህ ቀደም መንግስት በግልጽ እንዳስታወቀው አሁንም አሜሪካ በውስጥ ጉዳይ ላይ የምታደርገው ጣልቃ ገብነት ተገቢነት የሌለውና ተቀባይ የማይሆን መሆኑን ገልጾ፤ ኢትዮጵያን ማንም የውስጥ ጉዳይዋን እንዴት እንደምታስኬድ የሚያሳያት አካል ሊኖር አይችልም ሲል አስታውቋል።

መንግስት በትግራይ የሰብአዊ ድጋፍ ለመስጠት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር አብሮ ለመስራት ፍላጎት እና ቁርጠኝነቱን በማሳወቅ ሳይገታ ያልተቋረጠና የሙሉ ጊዜ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም መግለጫው አመልክቷል።

በአሜሪካ መንግስት የተላለፉ የቪዛ ገደቦችን እና ሌሎች ጉዳዮች የሁለቱን አገራት ለዘመናት የቆየ ገንቢ ትስስርን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ውሳኔ ነውም ሲል አስገንዝቧል።

ይህን መሰል ጫናዎች ከቀጠሉ ለዘመናት የቆየውን የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነቶች የሚጎዳ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ከአሜሪካን ጋር ያለውን ሁለትዮሽ ግንኙነት መልሶ እንዲገመግም የሚገደድ ይሆናል ብሏል።

በመጨረሻም መግለጫው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያጋጠሟትን ችግሮች በሕዝቦቿ አንድነትና ድጋፍ በመሻገር ሰላሟን አስጠብቃ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ ትቀጥላለች ሲል አስገንዝቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም