ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የህግ ትምህርትቤቶች የምስለ ፍርድ ቤት ውድድር ጎንደር ዩኒቨርስቲ አሸናፊ ሆነ

ድሬዳዋ ግንቦት 16/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤቶች መካከል የተካሄደው 5ኛው የምስለ ፍርድ ቤት ውድድር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲው በተዘጋጀ ውድድር የተሳተፉ የህግ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በሙሉ አሸናፊዎችና ተሸላሚዎች በመሆናቸው ይበረታታሉ ሲል የፌደራል ፍትህ፣ ህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

በአስራ ሁለት ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤቶች መካከል ለሶስት ቀን በተካሄደው የምስለ ፍርድ ቤት ውድድር ጎንደርና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ለፍጻሜ ቀርበው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አሸናፊ ተጠናቋል።

የውድድሩ አሸናፊ ከሆኑት የቡድን አባላት የ4ተኛ አመት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ተማሪ ዮሴፍ ነበሩ “ወድድሩ አስደሳችና በንድፈ ሀሳብ የተማርነውን በተግባር የተፈተንበት ነው” ብሏል።

ውድደሩ የሀገሪቱ የፍትህ ስርአትን ለማዘመን ተልዕኮ ለተሰጣቸው የህግ ተማሪዎች መደላደል የሚፈጥር መሆኑን ተናግሯል ።

“ወደፊት ጠበቃና ዳኞች ሆነን ህዝብን ስለምናገለግል ከታላላቅ የህግ ሙሁራን መሠረታዊ ዕውቀት ቀስመንበታል ”ብሏል።

ውድድሩ ትክክለኛ ችሎትን የሚመስል ገፅታ የተላበሰ በመሆኑ በእርግጥም በራስ መተማመኔ እንዲጨምር አጋጣሚው አድርጎኛል” ያለችው ደግሞ የውድድሩ ቡድን አሸናፊ የሆነችው ተማሪ ምህረት ሳምሶን ናት።

መድረኩ የተማሪዎችን በራስ መተማመን ያነፀና ተመራቂ ተማሪዎች አቅማቸውን ለማውጣት ያስቻለ መሆኑን ተናግራለች።

በውድድሩ 2ተኛ የወጣው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ አቦ በዳሶ በውድድሩ ለቀጣይ ሀገራዊ ተልዕኮው የሚሆን መሠረታዊ የተግባር ዕውቀት መቅሰማቸውን ገልጿል።

“በተለይም ተማሪዎች እርስበርስ በመተዋወቅና ልምድ በመካፋል ለዘላቂ መተባበርና ግንኙነት መሠረት ለመጣል አስችሎናል” ብሏል።

የፌደራል ፍትህ፣ ህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ማዳ ተማሪዎች በንደፈ ሃሳብ የቀሰሙትን እና በተግባር የተፈተሹበት ውድድር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የተቀናጀ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

“በውድድሩ የተሳተፉት በሙሉ አሸናፊዎች መሆናቸውን ገልፀው በውድድሩ የተሳታፊ ዩኒቨርሲቲ ቁጥር እንዲጨመር ይሰራል “ብለዋል።

በውድድሩ ላይ በእንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ የህግ ትምህርት ቤቶች ኮንሰርቲየም ሰብሳቢና የጎንደር ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሰለሞን ክፍሌ “ የሀገሪቱን የህግ ስርዓት አስተማማኝ የሚያደረጉ የህግ ተማሪዎች ውድድር የህግ ትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ ሁነኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል” ብለዋል።

ውድደሩ የህግ ስርዓተ ትምህርት እንዲስተካከል የራሱን ድርሻ እያበረከተ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም