ሃገር በቀል እውቀቶች ለዘላቂ ሰላምና አንድነት ሚናቸውን እንዲወጡ ማስቻል እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ሃገር በቀል እውቀቶች ለዘላቂ ሰላምና አንድነት ሚናቸውን እንዲወጡ ማስቻል እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ
ደሴ፤ ግንቦት 16/2013(ኢዜአ) ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ሀገር በቀል እውቀቶችን በማሳደግ ለዘላቂ ሰላምና አንድነት ሚናቸውን እንዲወጡ ማስቻል እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ስድስተኛው ዓለም አቀፍ የሀገር በቀል እውቀቶች አውደ ጥናት ትናንት ተጠናቋል፡፡
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ይስሃቅ በቀለ በአውደ ጥናቱ መድረክ "ሀገር በቀል እውቀቶች ለግጭት አፈታት ያላቸው ሚና" በሚል ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እንዳመለከቱት፤ሃገር በቀል እውቀቶች ግጭት የሚከሰተውን ጉዳት በዘላቂነት ለማስቆም ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል።
ብሔር ብሔረሰቦች እንደየባህልና እሴታቸው የሚከውኑት የሽምግልና እርቀ ሰላም ከፍርድ ቤቶች ይልቅ የተሻለ ዘላቂ መፍትሄ እንዳላቸው ጠቁመው፤ ለሀገር አንድነትና ሰላም ያላቸውን ሚና ለትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል።
የሽማግሌዎች ግጭቶችን ለመፍታት የሚጠቀሙት ጥበብ ለኢትዮጵያ ቀርቶ ለሌሎች ሀገራትም መትረፍ እንደሚችል የገለጹት ዶክተር ይስሃቅ እርቁ እንዳይፈርስ የሚያስገቡት ማህላና እርግማን ትልቅ አቅም እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
እየተሸረሸረ የመጣውን ድንቅ ባህልና እሴት በማስቀጠል ለትውልድ እንዲተላፍ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ፤ በመንግስት ተቋማት በኩል የሚደረገው ጣልቃ ገብነት ባህሉን እንዳይበርዝ ከአባቶች ጋር በቅንጅት መስራትም እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ባህልና ቋንቋ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ፍሬህይወት ባዩ "ዕድር ለሀገር አንድነትና ሰላም ያለው ፋይዳ" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ፤ ዕድር ብሔርን፣ እምነትን፣ ሀብታምና ድሃን መሰረት ሳያደርግ የተቋቋመ በመሆኑ የህብረተሰቡን ትስስር እንደሚያጠናከር ገልጸዋል።
ሲመሰረት በሐዘን ጊዜ የሚደርሰውን ጫና ለማቃለል ቢሆንም በሚደረጉ ውይይቶችና ግንኑነቶች ህብረተሰቡ እርስ በእርስ ተዋውቆ የአካባቢውን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ የጎላ ሚና እንዳለው አመላክተዋል፡፡
ዘመን ተሻጋሪ ሀገር በቀል እውቀቶች ለሀገር አንድነት፣ ሰላምና ዘላቂ መፍተሄ ለማበጀት ዓይነተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።
ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡም መንግስትና ባለድርሻ አካላት ባህልና እሴቱን ከሚያውቁ አባቶችና ምሁራን ጋር ተቀራርበው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
''የቱሪዝም ፍሰቱ ክፍ እንዲልና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አባቶቻችን ያወረሱን ሀገር በቀል እውቀቶች ተጠብቀው መቀጠል አለባቸው'' ያሉት ደግሞ በደቡብ ኮሪያ ዩኒቨርሲቲዎች የቱሪዝም መምህር ዶክተር አማረ ነጋ ናቸው፡፡
ሰላም ከሌለ ቱሪዝምም ሆነ ልማት እንደማይኖር ጠቁመው፤ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የኢትዮጵያዊያን እንግዳ አቀባበል፣ አክባሪነት፣ መልካም መስተንግዶና ሌሎችም ባህላዊ እሴቶችን መተግበር ጠቃሚ መሆኑን ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ባህላዊ መድሃኒት ህክምና አዋቂዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ሸህ አሊ አደም በበኩላቸው፤ ሀገሪቱ አሁን ከገጠማት ውስብስብ ችግር እንድትወጣና ለግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ምሁራን፣ አባቶች፣ ወጣችና ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
''ከተባበርና ከተደጋገፍን ችግሮችን መፍታት ቀላል ነው'' ያሉት፤ ሸህ አሊ የጋሞ አባቶች ባህልና እሴታቸውን ተጠቅመው ወጣቱ ሊፈጽመው የነበረውን ጥቃት እንዴት እንዳስቆሙት ማስተዋስ ብቻ በቂ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
''ሁላችንም ለሀገር አንድነትና ሰላም የምንችለውን አድርገን ከታሪክና ህሊና ተወቃሽነት መትረፍ ይኖርብናል'' ብለዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ የፌደራል፣ የደቡብ ወሎና የደሴ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን፣ የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የተሳተፉ ሲሆን 19 ጥናታዊ ጹሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡