በምርጫ ህግ ማዕቀፎችና የስርዓተ ፆታ ዙሪያ ለሴት ዕጩዎች የተዘጋጀ ስልጠና ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫ ህግ ማዕቀፎችና የስርዓተ ፆታ ዙሪያ ለሴት ዕጩዎች የተዘጋጀ ስልጠና ተጀመረ
አዳማ፤ ግንቦት 16/2013(ኢዜአ) በምርጫ ህግ ማዕቀፎችና የስርዓተ ፆታን ዙሪያ የሴት ዕጩ ተወዳዳሪዎችን አቅምና ክህሎት ለማዳበር የተዘጋጀ ስልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀመረ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀው ይሄው ስልጠና በተጀመረበት ወቅት በቦርዱ የስርዓተ ፆታ እኩልነት ዳይሬክተር ወይዘሮ መድሃኒት ለገሰ እንደገለጹት፤ ሴት ዕጩዎች ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር ብቁና ተወዳዳሪ የሚሆኑበት አቅም ለመገንባት እየተሰራ ነው።
በተለይም በመራጭነትና ተመራጭነት ሴቶች በንቃት እንዲሳተፉ ለማስቻል በምርጫ ህግ ማዕቀፎች፣ በህገ መንግስታዊ መብቶችና ዓለም አቀፍ ህጎች ዙሪያ በቂ ግንዛቤና ክህሎት እንዲኖራቸው ስልጠናው እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ምርጫው ነፃ ፣ ፍትሃዊ፣ ገለልተኛና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን እንዲሁም በሀገራዊ ጉዳይና በሰላም ግንባታ ላይ ሴቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በየደረጃው ያሉ የሴት አደረጃጀቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
በዚህም ቦርዱ የሴቶችን አቅምና ክህሎት ለማሳደግ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።
ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ከወትሮው በተለየ መልኩ በመራጭነት፣ በተመራጭነትና በምርጫ ታዛቢነት እንዲሳተፉ መደረጉ ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነትና ቅቡልነት የጎላ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ወይዘሮ መድሃኒት ገልጸዋል።
በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ላይ በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ ሴት ዕጩዎች እየተሳተፉ መሆናቸው ተመልክቷል።