ኢትዮጵያዊያን አንድነታችን በማጠናከርና ጫናዎችን በመቋቋም የህዳሴ ግደቡን ውሀ ሙሌትና ግንባታ ልናሳካ ይገባል…ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን አንድነታችን በማጠናከርና ጫናዎችን በመቋቋም የህዳሴ ግደቡን ውሀ ሙሌትና ግንባታ ልናሳካ ይገባል…ምሁራን
ዲላ ግንቦት 16//2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን የውስጥ አንድነታችን በማጠናከርና ጫናዎችን በመቋቋም የህዳሴ ግደቡን ውሀ ሙሌትና ግንባታ ልናሳካ ይገባል ሲሉ የዲላ ዩኒቨርስቲ ምሁራን አስታወቁ።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የስነ አስተዳደር ተመራማሪና መምህር መሳይ ፍቅሩ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የግድቡ ውሃ መያዝ በሱዳንና በግብጽ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳረፍ ይልቅ ዘርፈ ብዙ ጠቄሜታ እንዳለው ሀገራቱ እውነታውን ያውቁታል።
ሀገራቱድርድርን ተገን አድርገው የሚፈጥሩት ጫና በቀጣይ ኢትዮጱያ በአባያ ውሃ ላይ ያላትን ተጠቃሚነት ለመገደብ የሚደረግ የፖለቲካ ሴራ መሆኑን አመላክተዋል።
የህዳሴው ግድብ ውሃ መያዝና መጠናቀቅ ለሀገራችን ከሚያስገኝው ኢኮኖሚያዊ ጠቄሜታ ባሻገር ኢትዮጱያን በቀጠናው ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደሚያደርጋት ገልጸዋል።
የውስጥ አንድነታችንን በማጠናከር ጫናዎችን ተቋቁመን የህዳሴውን ግድብ እያጠናቀቅን በሄድን ቁጥር ከኢትዮጱያ ፍላጎት በተቃራኒ የተሰለፉ ምዕራባዊያንን ጨምሮ ግብፅና ሱዳን ወዳጅና አጋር መሆናቸው እንደማይቀር አስገንዝበዋል።
የግብጽና የምዕራባዊያን አሉታዊ ጫና ከግድቡ አልፎ በምርጫው ላይ በግልጽ እየታየ መሆኑን ያነሱት መምህር መሳይ በዲፕሎማሲው በተለይም ድርድሩን ወደ አፍሪካ ህብረት ለማምጣት የታየው ግልፅና ጽኑ አቋም በምርጫው ላይም መደገም እንዳለበት ጠቁመዋል።
ከምርጫው ታዛቢነት እንወጣለን በሚል የሚስተዋለው ጫና ዋና ዓላማ ኢትዮጱያ ጠንካራ መንግስት መስርታ ግድቡን ጨምሮ ሌሎች ልማቶችን በማጠናቀቅ በአከባቢው ጠንካራ ሃገር ሆና እንዳትወጣ ከመፈለግ የመነጨ መሆኑን አብራርተዋል።
ካለፉት ጊዜያት በተለየ 6ኛውን ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ነጻና ገለልተኛ ለማድረግ መንግስት ጠንካራ ተቋማትን ከመገንባት አንስቶ በርካታ ለውጦችን ማድረጉ እየታወቀ ከታዛቢነት ለመውጣት መወሰን ከምርጫ ውጭ ሌላ ፍላጎት እንዳለ በግልጽ እንደሚያሳይ አመላክተዋል።
የምርጫ ካርድ የወሰዱ ዜጎች በምርጫው በንቃት ከመሳተፍ ባለፈ ውስጣዊ አንድነታችን ለመከፋፈል የሚፈልጉ አካላትን በመከላከል ለሀገር እድገትና ሰላም በሃላፊነት መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
"የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጽያ ብቻ ሳይሆን ለአከባቢው ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ትስስር ሚናው የጎላ ነው " ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አለማየሁ አካሉ ናቸው።
ኢትዮጱያ ከግድቡ የምታገኝውን ኃይል ለጎረቤት ሃገራት በመሸጥ በድንበር ብቻ ተወስኖ ያለውን ግንኙነት ወደ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር በማሳደግ የቀጠናው የጋራ ልማትና ተሰሚነቷን እንደሚያጎላው አስረድተዋል።
በዓባይ ወንዝ ላይ በቀጣይ ያለንን ተጠቃሚነት ለመገደብ የሚደረግ ጫና መልኩን በመቀየር በምርጫው እየተስተዋለ መሆኑን ጠቁመው በግድቡ የውሃ ሙሌት ያሳየነውን ፅኑ አቋም በምርጫው በነቂስ ወጥተን በመሳተፍ ልንደግመው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የግድቡ ፍፃሜ ከዳር እስኪደርስ ጫናዎችን በጋራ ከመቋቋም ባለፈ ሁሉም ዜጋ ውስጣዊ አንድነቱን በማጠናከር ለሀገር ሰለምና እድገት የበኩሉን መወጣት እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።