ቀጥታ፡

አገራዊ ለውጡን ከዳር ለማድረስ ከመንግስት ጎን ሆነው ለሰላማቸው እንደሚደሩ በባሌ ዞን የጊኒር ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ

ጎባ ሀምሌ 26/2010 በአገሪቱ የተጀመሩ ለውጦችን ከዳር ለማድረስ ከመንግስት ጎን ሆነው የአካባቢያቸውን ሰላም እንደሚያስጠብቁ የባሌ ዞን ጊኒር ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ፡፡ ነዋሪዎቹ በአካባቢያቸው ሰላም ዙሪያ በጊኒር ከተማ ተወያይተዋል። ከውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ሼህ አብዱልጀዋድ ሀሰን  እንዳሉት ልዩነት በመፍጠር በህዝቦች መካከል  አለመተማመን እንዲኖር ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ በተለይ በሃይማኖት ሽፋን በጎባ ከተማና አካባቢዋ ሁከትና ግርግር ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው ይህም በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የለውጥና የይቅርታ ጉዞ የማይፈልጉ አካላት ሴራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለዘመናት ተከባብሮና ተዋዶ አብሮ የኖረውን  ህዝብ ለመከፋፈል እያደረጉት ያለውን ጥረትንም ኮንነዋል። አቶ ድርባ አበባ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው መንግስት ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ እየፈታ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡ "በተወሰኑ ቡድኖች ሰሞኑን በባሌ ጎባ የተፈጠረው የፀጥታ ችግሮች አሁን ቢረጋጋም ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አደራጃጀቶች ትኩረት ሰጥተው መስራት ይኖርባቸዋል" ብለዋል። ወጣቶችን በመወከል በውይይቱ ላይ የተሳተፈው ወጣት ሽመልስ ከተማ በበኩሉ አሳሳቾች አብዛኛውን ጊዜ እንደመሳሪያ የሚጠቀሙት ወጣቱን  መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡ መንግስትም ወጣቱን ኃይል ወደ ስራ በማስገባትና የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለይቶ በመፍታት በኩል የተጠናከረ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክቷል፡፡ ወጣቱ ኃይል አሳሳቾች በሚፈጥሩት አጀንዳ ስሜታዊ ከመሆን ተረጋግቶ ነገሮችን በሰከነ መልኩ በማጣራት ኃላፊነት በተሞላበት አግባብ መንቀሳቀስ እንዲችል በአደረጃጀታቸው በኩል እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ አቶ ሱሌይማን አብዱሰቡር የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው “ በዞኑ ህዝብ መካካል የሃይማኖት ግጭት እንዳለ ተደርጎ የሚነገረው መሰረተ ቢስ ወሬ መሆኑንና አጀንዳው ጥቅማቸው የተነካባቸው ቡድኖች የወጠኑት ሴራ መሆኑን ሊታወቅ ይገባል" ብለዋል፡፡ “ሁለቱም የሃይማኖት ተከታዮች ቤተ እምነታቸውን ጭምር ሲገነቡ ተጋግዘው መገንባታቸው ለአብሮነታቸው ትልቅ ማሳያ ነው” ብሏል፡፡ አቶ ሱሌይማን እንዳሉት ችግሩ እየተፈጠራ የሚገኘው በሀገሪቱ እየመጣ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ በሚሞክሩ ኃይሎች ነው፡፡ የጊኒር ከተማ ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ኡመር እንደተናገሩት መንግስት የህዝቡን  ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል በትኩረት እየሰራ ነው ፡፡ በመሆኑም ህዝቡ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት እሴቱን በማጠናከርና የአካባቢውን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም