በዓለም ገበያ የቡና ዋጋ ሲያሽቆለቁል የኢትዮጵያ ቡና ተፈላጊነቱን ጨምሯል- ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም ገበያ የቡና ዋጋ ሲያሽቆለቁል የኢትዮጵያ ቡና ተፈላጊነቱን ጨምሯል- ባለስልጣኑ
ዲላ፣ ግንቦት 15/2013 ( ኢዜአ) ጥራትን ለማሻሻል በተከናወኑ ተግባራት የዓለም የቡና ገበያ ሲያሽቆለቁል የኢትዮጵያ ቡና ተፈላጊነቱ መጨመሩን የቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ስነ ሕይወታዊ ባለሙያዎች ማህበርና በዲላ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተዘጋጀ በቡና ልማት ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት ተካሂዷል።
የፌደራል ቡናና ሻይ ባለሰልጣን ዋና ዳይሬክተርና የዲላ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አዱኛ ደበላ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓለም ገበያ የቡና ምርት በብዛት መግባቱን ተከትሎ ደንበኞች ወደ ጥራት ምርጫ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ270 ሺህ በላይ ሄክታር ያረጁ ቡናዎችን በአዲስ መተካትን ጨምሮ በምርት አሰባሰብ ወቅት በተከናወኑ ቁጥጥሮች የኢትዮጵያ ቡናን የጥራት ደረጃ ማሻሻል መቻሉን አስረድተዋል።
በተለይ ካፕ ኦፍ ኤክሰሌስን ጨምሮ የተለያዩ የገበያ አማራጮችን በመዘርጋት ከደረጃ በታች የሆኑ ቡናዎችን ከዓለም ገበያ በማውጣት ጥራት ያለውን ቡና በማቅረብ የተሻለ ዋጋ ማግኝት መቻሉን አስረድተዋል።
የዓለም የቡና ገበያ እያሽቆለቆለ ሲመጣ የኢትዮጵያ ቡና ተፈላጊነቱ መጨመሩን አስታውቀዋል።
አርሶ አደሩ አቅሙን አጎልብቶ ቡናውን ወደ ውጭ በቀጥታ መላክ እንዲችል የፖሊሲ ለውጥ ከማድረግ ባለፈ የኢትዮጵያ ቡና ከሀገር ሲወጣ የራሱን የንግድ ስያሜ እንዲይዝ በሀገር ውስጥና በውጭ የማስመዝገብ ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እየተከናወነ ያው ተግባር የኢትዮጵያ ቡና ከሌሎች ቡናዎች ጋር እንዳይቀላቀል ከማድረግ ባለፈ ምርቱን ብቻ ሳይሆን የንግድ ምልክቱን ጭምር በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንደሚያስችል አስረድተዋል።
ቡና የሃገር ኢኮኖሚ ዋልታና የማህበራዊ ትስስራችን መሰረት ከመሆኑ ባለፈ ስነ ምህዳርና ስነ ሕይወት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ስነ ሕይወት ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ቢቂላ ወርቅነህ ናቸው።
የማህበሩ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የምርምር ዘርፉ አካል በሆነው የቡና ልማት ዙርያ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አውደ ጥናት ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ማህበሩ ቡናን ጨምሮ የስነ ህይወት ተግዳሮቶችን በምርምር ለመቅረፍ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅርበት ከመስራት ባለፈ ቡናን በማበልጸግ የሃገር እድገት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አበባየሁ ታደሰ በበኩላቸው ቡና የሀገር ኢኮኖሚና የውጭ ምንዛሬ የጀርባ አጥንት ቢሆንም የቡናን ልማትና ጥራት ከማበልጸጉ ረገድ ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲው ችግሩን ለመቅረፍ በምርምር የተለዩ የቡና ዝሪያዎችን ለአርሶ አደሩ ከማሰራጨት ባለፈ በመስኩ እስከ 2ኛ ዲግሪ የማሰልጠንና የቡና ማበልጸግያ ማዕከል በማደራጀት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ጌዴኦና አጎራባች አካባቢዎች ጥራቱን የጠበቀ ቡና በማምረት የሚታወቅ መሆኑን ያነሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ልማቱን ለማስተዋወቅና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር አውደ ጥናቱ አስተዋጾው የጎላ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለሁለት ቀን በተካሄደው አውደ ጥናት ከ15 በላይ የምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የሀገር ውስጥና የውጭ ተመራማሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎችና ኩባንያዎች ተሳትፈዋል።