ቀጥታ፡

በመንግስት ብቻ የሚሰራ ልማት ባለመኖሩ ህዝቡ ዋነኛ የልማት አቅም መሆን አለበት- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

ግንቦት 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመንግስት ብቻ የሚሰራ ልማት ባለመኖሩ ህዝቡ ዋነኛ የልማት አቅም በመሆን ከመንግስት ጎን መሰለፍ አለበት ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ለአመያ ወረዳ ልማት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርና የልማት ማህበር ምስረታ ተካሂዷል።

በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጄር ጀኔራል ይልማ መርዴሳ፤ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝና ሌሎች የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በመንግስት ብቻ የሚሰራ ልማት ባለመኖሩ ህዝቡ ዋነኛ የልማት አቅም በመሆን ከመንግስት ጎን መሰለፍ አለበት ብለዋል።

የወረዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ለአመያ ከተማ ልማት ከመንግስት በጀት በተጨማሪ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩን ለማከናወን መነሳሳታቸው የሚያስመሰግናቸው ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስትም ከዚህ በጎ ተግባር ጎን በመቆም ለወረዳው ልማት በትኩረት ይሰራል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በአካባቢው ከፍተኛ ችግር የሆነውን የመንገድ መሰረተ ልማት ለመገንባት በመጭው ዓመት መስከረም ላይ ዲዛይን በመስራት ጨረታ እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።

የወረዳው ነዋሪ በሚችለው አቅም ሁሉ ከመንግስት ጋር ትብብሩን እንዲቀጥል ጠይቀው ይህም ድህነትን ለማስወገድ ዋነኛ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።

አካባቢው ትርፍ አምራች በመሆኑ አርሶ አደሩ ያለውን በመቆጠብ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን የሚያገኝበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ መንግስትም በየአመቱ በሽዎች የሚቆጠሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስመረቅ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአካባቢው ተወላጅ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጄር ጀኔራል ይልማ መርዴሳ፤ ልማት የሚመጣው መንግስት፣ ባለሃብትና ህዝብ በጋራ ተቀናጅተው ሲሰሩ ነው ብለዋል፡፡

አሁን የተጀመረው መልካም ተግባርም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ህዝቡ በሚችለው አቅም ሁሉ ከመንግስት ጎን እንዲሆን ጠይቀዋል።

የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ መገርሳ ዲሪብሳ በበኩላቸው የወረዳው ህዝብ በመንገድ እጦት ምክንያት ምርቱን ለገቢያ ማቅረብ አልቻለም ብለዋል።

ችግሩ ረጅም ጊዜ የፈጀ እንደመሆኑ መንግስት ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።

በይፋ ስራ የጀመረው የአማያ ወረዳ የልማት ማህበርም የ10 ዓመት እቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ቱሉ ተሾመ ናቸው።

በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ውስጥ ህዝቡን እርስ በርስ የሚያገናኙ የገጠር መንገዶችን ለመስራት ማቀዱንም ነው የገለጹት።

በተጨማሪም ምርታማነት እንዲያድግ የሚያደርጉ ተግባራትም በትኩረት ከሚሰሩ ስራዎች መካከል ናቸው ብለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎችም በወረዳው የተጀመረው እንቅስቃሴ ለዘመናት የቆየውን ችግር መፍታት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት ቃል በገባው መሰረት መንገዱን እንዲሰራላቸው ጠይቀው አካባቢው ሕዝብም በሚችለው አቅም ሁሉ ከመንግስት ጎን ለመቆም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን በዚህም 52 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ቃል ተገብቷል።

ከወረዳው ሕዝብ ደግሞ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል መገባቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም