ቀጥታ፡

5ተኛዉ የኢትዮጵያ የህግ ትምህርት ቤቶች ምስለ ፍርድ ቤት ውድድር እየተካሄደ ነው

ድሬዳዋ፣  ግንቦት 15/2013 (ኢዜአ) በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ 5ተኛዉ የኢትዮጵያ የህግ ትምህርት ቤቶች ምስለ ፍርድ ቤት ውድድር እየተካሄደ ነው።

ላላፉት ሁለት ቀናት በ12 የአገሪቱ የህግ ትምህርት ቤቶች መካከል በ6 ችሎቶች የዙር ውድድር ተካሂዷል ።


የዙሩን ውድድር በበላይነት ያጠናቀቁ የሁለት ዩኒቨርስቲ ቡዱኖች የመጨረሻውን የአሸናፊነት ደረጃ ለማግኘት የችሎት ክርክራቸውን ዛሬ ጀምረዋል ።


በውድድሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የፌደራል የፍትህ ህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ማዳ እንደተናገሩት በህግ ትምህርት ቤቶች መካከል የሚካሄደው ውድድር ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የቀሰሙትን ዕውቀት በተግባር የሚያሳዩበት ነው።


ተማሪዎቹ በውድድሩ ላይ የሚያደርጉት ክርክር ብቁ የህግ ባለሙያ ከማድረግ ባለፈ ውድድሩ ለህግ ትምህርት ጥራት መረጋገጥ መሠረታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል ።


ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የህግ ትምህርት ቤቶች ምስለ ፍርድ ቤት ውድድር ላይ የሚሳተፉት የመጀመሪያው ትውልድ ዩኒቨርስቲዎች ብቻ እንደነበሩ አስታውሰው አሁን ግን ሁሉም እንዲሳተፉ በማድረግ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከተመዘገቡት 19 ዩኒቨርስቲዎች መካከል 12ቱ የቅደመ ውድድር መስፈርት አሟልተው ተሳታፊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ባሉት አመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ይሳተፉ እንደነበሩ በማስታወስ ።


"ውድድሩ ሁሉም ተሳታፊዎች ዕውቀትና ክህሎት የሚገበዩበት፤ልምዳቸውን የሚለዋወጡበት በመሆኑ ሁሉም አሸናፊዎች ናቸው" ብለዋል።


የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡባህ አደም በበኩላቸው "ዩኒቨርስቲው ከሀገር አቀፍ ውድድሩ በርካታ ልምዶች የሚቀስምበት ብቻ ሳይሆን ለህዝብ እየሰጠ የሚገኘውን ነፃ የህግ አገልግሎቶችና ለህዝብ እያሰራጨ የሚገኘውን የሬድዮ የህግ ትምህርት አጠናክሮ እንዲቀጥል ያግዘዋል" ብለዋል።


ውድድሩ ተማሪዎች በተግባር የሚፈተኑበት ብቻ ሳይሆን ህብረ ብሔራዊነትን የሚያጎለብቱበት እንደሚሆን ተናግረዋል ።


የ5ተኛው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የህግ ትምህርት ቤቶች ምስለ ፍርድ ቤት ውድድር አሸናፊዎችን የሚለየው ወድድር በደመቀ ችሎትና ርዕሰ ጉዳይ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም