ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአለም አቀፉ የድሮን ኮንግረንስ ላይ በተጋባዥነት እየተሳተፈች ነው

ግንቦት 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቻይና ሸንዠን እየተካሄደ በሚገኘው 5ኛው አለም አቀፍ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ኮንግረንስ 2021 ኢትዮጵያ በክብር ተጋባዥነት እየተሳተፈች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ፣ ስዊዘርላንድና ፓኪስታን የዘንድሮ ኮንግረንስ የክብር ተጋባዥ ሀገራት ናቸው።

በቻይና የጓንዡ የኢትዮጵያ ቆንሲል ጀነራል አምባሳደር እውነቱ ብላታ “የሰው አልባ አውሮፕላንና የሰው ሰራሽ አስተውሎ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ትልቅ አቅም እየፈጠረ ነው” ብለዋል።

ቴክኖሎጂው በአቪየሽን፣ በጤና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ግብርና፣ አረንጓዴ ልማት፣ የመሬት አስተዳደርና የማዕድን ዘርፍ ውስጥ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፤ በኢትዮጵያና ቻይና ተቋማት መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሀመድ “በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ ውስጥ የተካተተውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እውን ለማድረግ የድሮን ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ድርሻ አለው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማሳደግና የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታዋን ለማፋጠን የድሮን ህግ ማውጣቷንና የጀማሪ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች በድሮን ቴክኖሎጂ ዘርፍ እንዲሰማሩ አስቻይ ሁኔታ እየፈጠረች መሆኗን ገልጸዋል።

በቻይና አፍሪካ ጥምረት በኩል ያለው የኢትዮ ቻይና ግንኙነትም ከቻይና የአቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ ሽግግር እያደረገ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በኮንግረንሱ ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ የኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ የተቋም መሪዎችና ምሁራን እየተሳተፉ ነው።

የቻይናና የውጭ ሀገራት ድርጅቶች ከ200 በላይ የዘርፉን አዳዲስ ምርቶች ይዘው ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም