ብልጽግና ፓርቲ የወጣቶችና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማጠናከር የጀመረውን የልውጥ ጉዞ ዳር ለማድረስ እንደሚሰራ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ የወጣቶችና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማጠናከር የጀመረውን የልውጥ ጉዞ ዳር ለማድረስ እንደሚሰራ ገለጸ
ጋምቤላ ግንቦት 14/2013 ( ኢዜአ ) በጋምቤላ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቶ ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ በክልሉ ኢታንግ ልዩ ወረዳ የምርጫ ክልል የሚወዳደሩ እጩዎች ዛሬ እራሳቸውን ለህዝብ አስተዋውቀዋል።
አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ብልጽግና ፓርቲ የለውጥ ኃይል የሆኑትን የወጣቶችና የሴቶችን ተሳትፎ በማጎልበት የኢትዮጵያን ለእድገትና ለውጥ ትንሳኤ ለማብሰር ይሰራል።
“የወጣቶችና የሴቶች ተሳትፎ ባልተካተተበት የማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ የለውጥ ምዕራፍ እውን እንደማይሆን ብልጽግና ፓርቲ ይገነዘባል” ብለዋል።
በመሆኑም ፓርቲው በተለይም በስድስተኛው ሀገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ የወጣቱን፣ የሴቶችን፣ የምሁራን ተሳትፎ ባካተተ መልኩ ለምርጫ መቅረቡን አስረድተዋል።
በክልሉ ምርጫው ፍህትዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በተለይም በወጣቶች የተጀመረው ሁለንታዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በዕለቱ የወረዳው ‘‘የአዶንግ ኪዮዎ’’ የወጣቶች የግንባታ ማህበር ፓርቲውን በመደገፍ ላዘጋጁት የትውውቅ መርሃ ግብር ስራ አስፈፃሚው ታላቅ ምስጋናቸውን አርቅበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አቶ ላክደር ላክባክ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ብልጽግና ዘር፣ቀላም ፣ብሄር ፣ቋንቋና እድሜ ሳይለይ ሁሉንም በአንድነት አካቶ እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራ ፓርቲ ነው።
ስለሆነም ፓርቲው ምርጫው ሰላማዊና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሁኖ እንዲጠናቀቅ ለጀመራቻው ስራዎች መቃናት በተለይም ወጣቶች ተሳፏቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በወረዳው ‘‘የአዶንግ ኪዮዎ’’ የወጣቶች የግንባታ ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ኡቦንግ አበላ መጪው ስድስተኛው ሀገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጿል።
በዕለቱ የእጩዎች የትውውቅ መድረኩን ያዘጋጁት ማህበሩ ለብጽግና ፓርቲው ያለውን አጋርነት ለማሳየት መሆኑን ተናገሯል።