የሀገር በቀል እውቀትን ለማጎልበት ስርዓተ ትምህርት ተቀርጾ እየተተገበረ ነው-ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር በቀል እውቀትን ለማጎልበት ስርዓተ ትምህርት ተቀርጾ እየተተገበረ ነው-ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ
ባህርዳር ፤ ግንቦት 14/2013 (ኢዜአ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሀገር በቀል እውቀትን ለማጎልበት ስርዓተ ትምህርት ተቀርጾ እየተተገበረ እንደሚገኝ የሳይንሰና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ አስታወቀ፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በሀገር በቀል እውቀት ላይ የተኮረ ስድስተኛው ዓለም አቀፍ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።
ፕሮፌሰር አፈወርቅ በአውደ ጥናቱ መድረክ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ያላት ባህልና እሴት ከራስ አልፎ ለሌሎች ሀገራት መትረፍ የሚችል ነው፡፡
ከእሴቶቹም መካከል በግጭት አፈታት፣ በባህል መድሃኒት ቅመማ፣ በዕደ ጥበብ፣ በመከባበር፣በአብሮነትና በመረዳዳት ጉዳዮች ያለው ትውፊት ዓለምን የሚያስደምም መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሀገራዊ አንድነትና ሰላም፣ ብሄራዊ መግባባት፣ እርቀ ሰላምና ሌሎች ሀገር በቀል እውቀቶችን ያካተተ የኢትዮጵያ ባህል እሴት በስርዓተ ትምህርት ተቀርፆ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።
ይህም በሃሰት ትርክት ህብረተሰቡን እርስ በርስ ለማጋጨት የሚሰሩ የጥፋት ኃይሎችን በአዲሱ ትውልድ ለመመከት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
አባቶች ጠብቀው ያቆዩን ሀገር በቀል እውቀትና ትውፊት ሳይሸራረፍ ለትውልድ እንዲተላለፍ በተለይም የከፍተኛ ትምህርትተቋማት ሃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ሚንስቴሩ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በጥናትና ምርምር ታግዞ በቀጣይ አስር ዓመታት አንዱ የህብረተሰቡን ችግር መፍቻ እንዲሆን ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ በበኩላቸው፤ ሀገራችን በተፈጥሮ ሃብት ብቻ ሳይሆን በሰው ሰራሽ፣ ታሪካዊ፣ ሐይማታዊና ባህላዊ እሴቶች የታደለች መሆኗን ዓለም የመሰከረው ጉዳይ ነው ብለዋል።
ባህልና እሴቱ ተጠብቆ ሰላምና አንድነት እንዲጎለበት ዩንቨርሲቲው የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው ለሰላም ግንባታ ከደቡብ ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብና ደሴ ከተማ አስተዳደሮች በተጨማሪ ከአፋር ክልል ጋር በቅንጅት እየሰራን መሆኑን አስረድተዋል።
"አንድነትና ሰላም፣ ብሔራዊ መግባባትና መከባበርን የሚያለብቱ ሀገር በቀል እውቀቶች ለትውልድ እንዲተላለፉም ከሐይማኖት አባቶች፣ ሀገር ሽማግሌዎችና ሌለችባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራን ነው" ብለዋል፡፡
ትውልዱ የአባቶችን ምክር በመስማትና በእያዳንዱ ጉዳይ ላይ ምክንያታዊ በመሆኑ ለሀገሩ ሉዓላዊነት መከበር ዘብ ሊቆም እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
እየተሸረሸረ የመጣው የወሎ የመከባበር፣ የመቻቻል፣ የሰላምና የፍቅር እሴት እንዲጎለብትና ለትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም በየደረጃው ሊሰራ ይገባል ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚሰሩ የውጭና ውስጥ ጠላቶች አልሳካላቸው ሲል በሐይማኖት ለማጋጨት የማያደርጉት እንደሌለ የተናገሩት አቶ ሰይድ ህብረተሰቡ በተደራጀ አግባብ በመመከት የአባቶቹን ታሪክ መድገም አለበት ብለዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው አውደ ጥናት 19 ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው ይጠበቃል።
በአውደ ጥናቱ የፌደራል፣ ክልል፣ ደቡብ ወሎና ደሴ ከተማ አስተዳደር ፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ አመራሮች፣ ምሁራን፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌለች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።