ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊነት የጠንካራ አንድነት መገለጫ መሆኑን ትውልዱ እንዲገነዘብ የበለጠ መሰራት ይገባል

ግንቦት 14/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊነት የጠንካራ አንድነት መገለጫ መሆኑን ትውልዱ እንዲገነዘብ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የአገር ሽማግሌዎችና አስተያየት ሰጪዎች ጥሪ አቀረቡ።

"የኢትዮጵያ ሳምንት" በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ እየተከበረ ይገኛል።

በመድረኩም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ልዩ መገለጫዎቻቸውንና የተፈጥሮ ሃብቶቻቸውን በቅርጻ ቅርፆች፣ በሥዕል እና በተንቀሳቃሽ ምሥል ለእይታ አቅርበዋል።

ኢዜአ በስፍራው በመገኘት ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች አንዳንድ ግለሰቦችና ፖለቲከኞች የኢትዮጵያዊነትን እሴት የሚሸረሽሩ አመለካከቶችን ሲያራምዱ እንደሚስተዋል ገልጸዋል።

ይህ ደግሞ በባህል፣ በታሪክ፣ በሃይማኖት እንዲሁም በጋብቻ ተሳስሮ ለዘመናት የኖረውን ሕዝብ አብሮነት የሚጎዳ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ባሕላዊ እሴቶችና ጸጋዎችን በማወቅና በማስተዋወቅ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ብዙነህ ፎሌ የኢትዮጵያን ሕዝቦች እሴት በሚያሳይ አውደ ርዕይ እየተከበረ ያለው "የኢትዮጵያ ሳምንት" አንድነትንና አብሮነትን በማጎልበት ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

አውደ ርዕዩ ማንኛውም ዜጋ የኢትዮጵያን ባህልና የተፈጥሮ ሃብቶች እንዲሁም አብሮነት በአጭር ጊዜ እንዲገነዘብ ያስችላል ነው ያሉት።

ዜጎች ኢትዮጵያ የብዝሃ ባህልና እሴት ባለቤት መሆኗን አውቀው ተከባብረውና ተቻችለው እንዲኖሩ እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

ወጣቶች ስለ አገራቸው ባህል፣ እሴትና የተፈጥሮ ሃብት እንዲያውቁ የተለያዩ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው የገለፀችው ደግሞ የጋምቤላዋ ወጣት አጁሉ ዱዋል ናት።

የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ወላጆች ስለ ፍቅርና አብሮነት ለወጣቶች ማስተማር እንዳለባቸው ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም