የፍትህ አካላት ለምርጫው ስኬታማነት ሚናቸውን በሚገባ ሊወጡ ይገባል-- የፍትህ ስልጠናና የህግ ምርምር ማዕከል - ኢዜአ አማርኛ
የፍትህ አካላት ለምርጫው ስኬታማነት ሚናቸውን በሚገባ ሊወጡ ይገባል-- የፍትህ ስልጠናና የህግ ምርምር ማዕከል
ግንቦት14/2013 (ኢዜአ) ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፍትህ አካላት ሚናቸውን በሚገባ ሊወጡ እንደሚገባ የደቡብ ክልል የፍትህ ስልጠናና የህግ ምርምር ማዕከል አሳሰበ፡፡
ማዕከሉ በክልሉ ከሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ መርማሪ ፖሊሶችና ዐቃቢያን ህግ በወንጀል ምርመራ ስርዓት ዙሪያ በአርባ ምንጭ ከተማ ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡
በስልጠናው መድረክ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ አዴቶ እንደገለጹት፤ መጪው ምርጫ ለልማትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ ነው።
ምርጫው ሰላማዊ፣ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተአማን ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፍትህ አካላት በመደገፍ ሚናቸውን በተገቢው ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በአዋጅ የተቋቋመው የፍትህ ስልጠናና የህግ ምርምር ማዕከሉ ለዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች የማስፈጸም አቅማቸውን ከመገንባትም በላይ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡
ማዕከሉ እስካሁን በክልሉ ለሚገኙ ከ10ሺህ በላይ የህግ ባለሙያዎችና አመራሮች የክህሎት ስልጠና በመስጠት የበኩሉን መወጣቱን አውስተዋል፡፡
ይህም በባለሙያዎችና አመራሮች ዘንድ የሚስተዋሉ የዕውቀት፣ክህሎት፣አመለካከትና የስነ-ምግባር ክፍተቶችን ለማስተካከል ማገዙን ተናግረዋል፡፡
የአሁኑ ስልጠናው በወንጀል ምርመራ አተገባበር ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
በስልጠናው መድረክ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሳሙኤል ምትኬ በበኩላቸው ፤ አንድን የወንጀል ምርመራ ውጤታማ ሊያደርግ የሚችለው የታክትክና ቴክኒክ ምርመራ በአግባቡ ስከናወን ነው ብለዋል፡፡
ይህም ከአንድ ወንጀል ጋር በተያያዘ ሰዎችን የተለያዩ ጥያቄዎችን በመጠየቅ እንዲሁም በሳይንሳዊ መንገድ ወንጀሉ በተፈጸመበት ስፍራ በመሄድ በሚደረግ ምርመራ የሚገኝ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፍትህ አካላት ዕውቀቱ ቢኖራቸውም የክህሎት ክፍተቶች በስፋት የሚስተዋልባቸው በመሆኑ ስልጠናው በዐቃቢያን ህግና መርማሪ ፖሊስ መካከል የነበረውን ክፍተት እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡
ስድስተኛ ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ መሆን መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ገልጸው ለዚህም ማንኛውም ሰው የምርጫ ህግ ማዕቀፎችን ማክበር ይጠበቅበታል ብለዋል።
የፍትህ አካላትም በስልጠናው በመታገዝ በምርጫው ሂደት የሚያጋጥሙ ጉዳዮችን በፍጥነት መርምሮ ለውጤት ማብቃት እንዳለባቸውም አቶ ሳሙኤል ጠቁመዋል፡፡