በአማራ ክልል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በትምህርት ቤቶች ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በትምህርት ቤቶች ሊካሄድ ነው
ባህር ዳር፤ ግንቦት 14/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ለአንድ ወር የሚቆይ ተማሪዎች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለማካሄድ ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታወቀ።
በወሳሽ ኩነት ምዝገባ ዙሪያ ከመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙ ያዎችና አመራሮች ጋር በዳንግላ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሄዷል።
በምክክር መድረኩ የኤጀንሲው የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር አቶ በተግባር እንየው እንደገለጹት፤ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በክልሉ በታሰበው ልክ እየተከናወነ ባለመሆኑ በትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ኩነት የመመዝገብ ስራ ነገ ይጀመራል።
ኤጂንሲው ባለፉት ዘጠኝ ወራት 508 ሺህ 962 የተለያዩ ኩነቶችን ለመመዝገብ አቅዶ ማሳካት የቻለው የዕቅዱን 51 በመቶ ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የአመራሩ ትኩረት ማነስ፣ የምዝገባ ስራው በተደራቢነት መካሄድ፣ ወቅታዊ ሁኔታው፣ የበጀት ዕጥረትና የህብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ ለአፈፃፀሙ ማነስ በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በተደራጀ አግባብ ስራው መከናወን እንዳለበት አመልክተው ፤ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግና የምዝገባ ስራውን በባለቤትነት የሚያከናውን የሰው ኃይል መሟላት እንዲሁ።
ለዚህ ይረዳ ዘንድም ኤጀንሲው ባህር ዳርን ጨምሮ በተመረጡ 11 ከተሞች በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከግንቦት 15/2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
ምዝገባው በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ ለትምህርት አመራሩ ስልጠና መሰጠቱንና 13 ሺህ የክብር መዝገቦችን ግብዓት የሟሟላት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።
ምዝገባውን ለሚያከናውኑ 540 ወጣቶችም ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጎ የስራ ስምሪት መደረጉን አስረድተዋል።
ለአንድ ወር በሚቆየው መረ ግብር 410 ሺህ 872 ተማሪዎች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በማከናወን የልደት የምስክር ወረቀት እንደሚሰጣቸው አመልክተዋል።
የምዝገባ ስራው በውጤታማነት እንዲጠናቀቅም የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የድርሻቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
''የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስራዎችን በመረጃ ላይ ተመስርቶ ለማከናወን ፋይዳው የጎላ ነው'' ያሉት ደግሞ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ናቸው።
የክልሉ የልማት ችግር በዘላቂነት የሚፈታው በየደረጃው ያለው አመራርም ሆነ ህብረተሰቡ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም ተረድቶ ማከናወን ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል።
ባለድርሻ አካላት በተቀናጀ አግባብ ስራውን በማከናወን የክልሉን ልማት እንዲፋጠን መስራት እንደሚኖርባቸው ያመለከቱት አቶ ግዛቸው ፤ ህብረተሰቡም በየቀኑ የሚፈፀሙ ኩነቶችን በማስመዝገብ የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን ተቋማትም ህብረተሰቡ ስለወሳኝ ኩነት ምዝገባ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው የተግባቦት ስራን ትኩረት ሰጥተው ሊያከናውኑ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ኤጀንሲው የምክክር መድረኩን ያዘጋጀው ከፕላን ኢንተርናሽናል ጋር በመተባበር እንደሆነ ተመልክቷል።