በመዲናዋ ከ135 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ 74 ፕሮጀክቶች ተመረቁ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ከ135 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ 74 ፕሮጀክቶች ተመረቁ
ግንቦት 14/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ከ135 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ 74 የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡
ክፍለ ከተማው በበጀት ዓመቱ 83 ነባር እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለማስገንባት አቅዶ የተጠናቀቁትን 74 ፕሮጀክቶች ዛሬ አስመርቋል፡፡
ለምረቃ ከበቁት ፕሮጀክቶች መካከል ትምህርት ቤት፣ የስፖርት ሜዳዎች፣ የጤና ተቋማት፣ የወጣቶች ማዕከል እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ይገኙበታል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለሰ አለሙ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ መጨረስ ከለውጡ ትሩፋቶች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
"ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጀምሮ ፕሮጀክቶችን እየፈተሹ አመራር በመስጠት ለፍጻሜ ማብቃት ለውጡ ያመጣቸው ፍሬዎች ናቸው" ሲሉ ነው የገለጹት።
በመዲናዋ ከታቀዱ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል ለምረቃ የበቁት የዚሁ አካል መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ለፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ በመዲናዋ ከኅብረተሰቡ ጋር በመወያየት ሕዝቡን ማዕከል ያደረገ ዕቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን በምክንያትነት ገልጸዋል።
አያይዘውም የኢትዮጵያን የማደግና የመበልጸግ ፍላጎት ማንም ሊገታው እንደማይችል የገለጹት አቶ መለሰ ለዚህም መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በኢትዮጵያ ላይ ከውጭና የሚሰሙ ድምፆች እየተበራከቱ መምጣታቸውንና ይህም የኢትዮጵያ የመነሳት ዘመኗ ማሳያ እንደሆነ አክለዋል።
አገራዊውን ምርጫና ሁለተኛው ዙር የሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት ስራ በስኬት እንዲጠናቀቅ መላው ሕዝብ ሀላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሽታዬ መሀመድ በበጀት ዓመቱ 44 ነባር እና 39 አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ታስቦ 74 ተጠናቀው ለአገለግሎት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
በጤናው ዘርፍ የአራት ጤና ጣቢያዎች ግንባታ እና የአንድ ሆስፒታል እድሳት ሥራ ተጠናቆ ወደስራ እንዲገቡ መደረጉንም አክለዋል።
በቀሪ የበጀት ዓመቱ ወራት በተለያየ ምክንያት ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።
የክፍለ ከተማው ኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ቴኑስ ገላና በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ ከተያዙት የልማት ፕሮጀክቶች መካከል 15 ትምህርት ቤቶችና አምስት የስፖርት ሜዳዎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሁለት ቤተመጻህፍት፣ አራት የወጣት ማዕከላት እንዲሁም በርካታ አገልግሎት መስጫ ተቋማት መካተታቸውንም ገልጸዋል።
ፕሮጀከቶቹ ከኅብረተሰቡና በተደጋጋሚ ሲቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎችን የመለሱ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በምረቃ መርሃ ገብሩ ፕሮጀክቶቹ በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ ላደረጉ አመራሮች፣ ድርጅቶችና ሠራተኞች የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡