ቀጥታ፡

መንፈሳዊ ትምህርት ቤቱ 170 ተማሪዎችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/ 2013 ዓ.ም(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገስት በዓታ ለማርያም ገዳም የመምህራንና ቀሳውስት ማሰልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት 170 ተማሪዎችን አስመረቀ።

በመንፈሳዊ የትምህርት ዘርፍ ሰልጥነው ለምረቃ ከበቁት መካከል 115 በአጫጭር የስብከት እንዲሁም 55 የዕጩ መምህርነት ትምህርት የተከታተሉ መሆናቸው ተገልጿል።

በምረቃ መርሐግብሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስን ጨምሮ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

ተማራቂዎቹ በአዲስ ኪዳን፣ በብሉይ ኪዳን እና በመጻሕፍተ ሊቃውንት እንዲሁም በቅኔ ትምህርት ዘርፍና በሌሎች የቤተክርስቲያኗ የትምህርት ዘርፎች ስልጠና የተከታታሉ ናቸው።

በዚህ ወቅት ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ተመራቂዎች በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ትውልድ ለማነፅና መልካም ዜጋ ለመፍጠር እንዲጠቀሙበት መልዕክታቸውን አስተላላፈዋል፡፡

የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መልከጼዴቅ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ 'ለምድር ጨው' በመሆን መልካም ተግባር መፈጸምና ሌሎችንም ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ምሩቃኑም ትውልዱ በመልካም ስነ-ምግባር የታነጸ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አገሩን የሚወድ ትውልድ መፍጠርና በሃይማኖቱ ጸንቶ የሌሎችን እምነት የሚያከብር መልካም ዜጋ መፍጠር ተቀዳሚ ግባቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገስት በዓታ ለማርያም ገዳም የመምህራንና ቀሳውስት ማሰልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ማስተማር የጀመረው በ1925 ዓ.ም ሲሆን እስካሁን በመንፈሳዊ ትምህርት 27 ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ መምህራንን፣ ካህናትና ዲያቆናትን ማፍራቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም