ቀጥታ፡

የዲላ ከተማ እድሮች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

ዲላ ሀምሌ 26/2010 በዲላ ከተማ የሚገኙ እድሮች ከምዕራብና ምስራቅ ጊጂ ዞኖች ለተፈናቀሉ ወገኖች 285 ሺህ ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡ የከተማው እድሮች ሰብአዊ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገዛኸኝ ሙሉጌታ በከተማው በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ተገኝተው ድጋፉን  ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት 13 እድሮች ለወገን ደራሽ ወገን ነው በሚል ድጋፉን አድርገዋል ። "እደሮቹ ባደረጉት 285 ሺህ ብር ድጋፍ ብርድ ልብስ፣ ምንጣፍና የመመገቢያ ቁሳቁስ ገዝተው ለተፈናቃዮች እንዲደርስ ተደርጓል" ብለዋል ። በከተማዋ ከ50 በላይ እድሮች እንደሚገኙ በመግለጽ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በከተማዋ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮችና ከእድር አባላት የተሰበሰቡ አልባሳትም በድጋፉ በተጨማሪነት  መካተቱን ጠቅሰዋል ። "ተፈናቃዮች አሳሳቢ ሁኔታ ወስጥ እንደሚገኙ ተመልክተናል" ያሉት የአስተባባሪ ኮሚቴው ሒሳብ ሹም አቶ ጌታሁን በቀለ በድጋፍ ማሰባሰብ ወቅት የእድር አባለቱ የነበራቸው ተነሳሽነት ከፍተኛ እንደነበር ገልፀዋል ። በከተማዋ የሚገኙ እድሮች በጥምረት ቢንቀሳቀሱ ለከተማዋም ሆነ ለአካባቢው የሚጠቅሙ በርካታ ተግባራትን የማከናወን አቅም እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ጌታሁን "የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው ተመልሰው የተረጋጋ ኑሮ እስኪጀምሩ ድረስ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል ፡፡ የኮሚቴው ገንዘብ ያዠ ወይዘሮ ውዴ ደጉ በበኩላቸው ዜጎች ተፈናቅለው ለእንግልት በመዳረጋቸው ማዘናቸውን ገልፀው፣ በተለይ ነፍሰጡርና ወላድ እናቶች ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ መመልከታቸውን አስረድተዋል ፡፡"ወደፊትም ባለን አቅም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን " ብለዋል ። የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ይመኑ ዳካ በበኩላቸው እድሮችና ሌሎች በማህበራዊና መንግስታዊ መዋቅሮች ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች እያደረጉ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፡፡ በዲላ ከተማ ከ62 ሺህ በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች ተጠልለው እንደሚገኙ የገለፁት ከንቲባው መንግስት እያደረገ ያለው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ከተቋማትና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም