ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቀጣናውን በአረንጓዴ ልማት ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት ሊደገፍ ይገባል ተባለ

ግንቦት 14፤2013 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ ቀጣናውን በአረንጓዴ ልማት ለማስተሳሰር እያደረገች ያለውን ጥረት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊደግፈው እንደሚገባ ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ የሆነ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ተናገሩ።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የ2013 የአረንጓዴ አሻራ ትግበራን አስመልክተው በኢትዮጵያ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ገለጻ አድርገዋል።

ሚኒስትሩ በገለጻቸው የአረጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ፋይዳና አተገባበርን በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አማካኝነት ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም አካባቢ ጥበቃ ያላትን ቁርጠኛ አቋም ገልጸዋል።

በመድረኩ የተገኙት የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትም ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ቀጣናውን በአረንጓዴ ልማት ለማስተሳሰር እያደረገች ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን የኢትዮጵያ ጥረት እንዲደግፍም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ጉልህ አበርክቶ ማድረጓን አስታውሰዋል።

ይህን አበርክቶ በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት ለመድገም እየጣረች መሆኑንም ነው ያወሱት።

እስራኤል ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት ከሚሰጡ አገራት መካከል ተጠቃሽ መሆኗን በመግለጽ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ትሰራለች ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የቀጣናው ተወካይ ፓትሪዚያ ካላብሮ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እንደ ሶማሊያ ያሉ ከፍተኛ ድርቅ ከሚከሰትባቸው አገራት ጋር በአረንጓዴ ልማት ለመተሳሰር የምታደርገው ጥረት የሚደገፍ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

''የአረንጓዴ ልማት ስራ የሁላችንም ለሆነችው ምድር የሚሰራ በመሆኑ ድንበር ተሻጋሪ መሆን አለበት'' ነው ያሉት።

ከዚህ አንጻር ሁሉም የዓለም ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ጥረት መደገፍ እንዳለበት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የዩክሬን አምባሳደር አማካሪ ዶክተር አሌክሳንደር ዙብ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት የሰጠችው ትኩረት እውን እንዲሆን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋራ መቆም እንዳለበት ተናግረዋል።

አገራቸው ዩክሬን ፕሮጀክቱን እንደምትደግፈውም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በአረንጓዴ ልማት ለመተሳሳር የምታከናውነው ተግባር ከምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚመነጭ ነው ያሉት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ ናቸው።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በየትኛውም የጎረቤት አገር የሚከሰት ድርቅ ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ማድረሱ አይቀሬ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።መርሃ ግብሩ "መገፋፋት ሳይሆን መተባባር" የሚለውን የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ እሳቤ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም