ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢኒስቲትዩት ኅብረተሰቡ ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ትኩረት እንዲሰጥ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13 ቀን 2013 (ኢዜአ) የተፈጥሮና የአካባቢ ጥበቃ ችግሮች ለመከላከል ኅብረተሰቡ የብዝሀ ሕይወት እንክብካቤ ሥራን ሊያጠናክር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢኒስቲትዩት ጠየቀ።

"እኛ ለተፈጥሮ የመፍትሔ አካል ነን!" በሚል መሪ ሀሳብ 20ኛው ዓለም አቀፍ የብዝሃ ሕይወት ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡

በዓሉን በማስመልከት ከባለድርሻ አካላት ጋር የፓናል ውይይት አካሂዷል።

የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማርዮ በውይይት መድረኩ እንደተናገሩት፤ ዓለም የተጋረጡባትን የተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ ችግሮች ለማቃለል ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

እ.አ.አ በ2030 የምግብ አቅርቦት ፍላጎት አሁን ካለው በግማሽ ሊጨምር እንደሚችልና የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትም 30 በመቶ ጭማሪ ማሳየት እንዳለበት ጥናቶች እንደሚያሳዩ ጠቁመዋል፡፡

ይህንን ለማስተካከል ያለው አማራጭ የብዝሀ ሕይወትን መጠበቅና መንከባከብ መሆኑን አስገንዝበው፤ ኢትዮጵያ እነዚህን ችግሮች መከላከል የሚያስችሏትን ሥራዎች ስታከናውን መቆየቷንም ተናግረዋል፡፡

በፓናሉ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶክተር ደቢሳ ለሚሳ የተሟላ ጥናትና ምርምር ባለማካሄድና ያደጉ አገራትን ተሞክሮ ባለመቅሰም ሳቢያ የብዝሀ ሕይወት ክምችት ኖሯቸው በድህነት ውስጥ የሚኖሩ በርካታ አገራት መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያም ከእነዚህ አገራት ተርታ እንደምትመደብም ገልጸዋል።

በመሆኑም ይህን ችግር ለመፍታት የተቀናጀ አሠራር መተግበርና አሁን ለዘርፉ ከተሰጠው ትኩረት በላይ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ6 ሺህ የሚበልጡ የብዝሀ ሕይወት ዘር ያላትና ከእነዚህም 10 በመቶው በሌሎች አገራት የማይገኙ ብርቅዬ አዝርዕትና ተክሎች ባለቤት እንደሆነች ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ በበኩላቸው፤ "የኢትዮጵያን የብዝሀ ህይወት በነበረበትና በተሻለ ሁኔታ ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ሉዓላዊነትን ከማስከበር ተነጥሎ ሊታይ አይገባም" ብለዋል፡፡

መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም እየተለመደ መምጣቱም በመድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም