ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን 'በውስጥ ጉዳዮቻችን ላይ የተዘረጉ የውጭ እጆች ይነሱ' ሲሉ ጠየቁ

ግንቦት 13 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን 'በውስጥ ጉዳዮቻችን ላይ የተዘረጉ የውጭ እጆች ይነሱ' ሲሉ ጠየቁ።

"ኢትዮጵያ በዘመነ ክብሯ ሉዓላዊነቷን የሚገሰስ የትኛውንም ኃይል አሜን ብላ የተቀበለችበትና ያጎነበሰችበት ዘመን አልነበረም፤ አይኖርምም" ሲሉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ንቅናቄ አካሂደዋል።

ኢትዮጵያዊያን የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በያሉበት ሆነው ድምፃቸውን የሚያሰሙበት መርሃ ግብር በመላ ኢትዮጵያ ተካሂዷል።

"እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ" በሚል መሪ ሃሳብ በያሉበት ሆነው ለአንድ ሠዓት መልዕክታቸውን የሚያስተላልፉበት መርሃ ግብር በሀገር ፍቅር ቲያትር ቅጥር ግቢ በይፋ ተጀምሯል።

"ብሔራዊ ክብር በሕብር" የሚል ስያሜ ያለውን ይህን ንቅናቄ ያዘጋጁት የማሕበረሰብ አንቂዎች፣ አርቲስቶች፣ የሲቪክ ማሕበራትና ታዋቂ ግለሰቦች ናቸው።

"ግድቡ ገንዘቤ፣ ዓባይ ወንዜ!፣ ዓባይ ጸጋችን ነው፣ ኢትዮጵያ አትደፈርም አንንበረከክም" የሚሉ መፈክሮችንም አስተጋብተዋል።

'ክብርና ሉዓላዊነታችንን አትንኩ የምንለው በአያቶቻችንን መስዋዕትነት የታፈረች፣ የተከበረች እና በዋጋ የተረከብናት አገር በመሆኗ ነው' ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል አዘጋጆቹ።

የንቅናቄው መልዕክት በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች ተላልፏል።

"ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ነፃነትን ያስተማረች፤ አልገዛም ባይነትን በተግባር ያሳየች፤ የነፃነት ተምሳሌት ሀገር ነች" ሲሉም ተናግረዋል።

"ከአያቶቻችንና የወረስነው ልበ ሙሉነት፣ ሌላውን ማክበርና ቀና ብሎ መራመድን እንጂ ለፍርሃት ማቀርቀርን አይደለም" ብለዋል።

ከአዘጋጆቹ አንዷ የሆነችው ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ "ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋዕትነት የታፈረች፣ የተከበረች በደም ዋጋ የተረከብናት ናት" ስትል ተናግራለች።

"ለዘመናት የኖርንበትና የተጋመድንበትን የአንድነት መሰረት የሚገዳደርና ክብራችንን የሚገስ ተግባራትን አጥብቀን እንቃወማለን" ብላለች።

መላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያለ ሰቀቀን የሚኖሩበት ከተማና ገጠር መፍጠር፣ ህግና ስርዓትን ማስከበር፣ ዳር ድንበር መጠበቅ የመንግስት ተቀዳሚ ሀላፊነት መሆኑንም ገልጻለች።

በውስጥ ያሉ ልዩነቶች ሳይገድቡ አገር ለማኖርና ለማዝለቅ በአንድነት እንቆማለን፤ ዓባይን እያቀናን ያለነው የእናቶቻችንን ዓይን በጢስ ከሚያጠፋ የማይገፋ ኑሮ ለመገላገል ነው ስትል ተናግራለች።

ምርጫው ሠላማዊ፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆንና በሕዝብ የሚመረጠው መንግስት ከመላው ዓለም ጋር የሚኖረው ግንኙነትና ውሳኔዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ የጸደቀ መሆን እንዳለበትም አክላለች።

የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ የሌላውን አገር መብት መንካትና መግፋት አለመሆኑን ሁሉም ሊረዳ እንደሚገባም ተናግራለች።

ኢትዮጵያዊያን ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ሠላም በየዘመናቱ ልጆቻቸውን የገበሩ መሆናቸውን በመረዳት ሁሉም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም በንቅናቄው ጥሪ ቀርቧል።

የንቅናቄ መርሃ ግብሩ በአደባባዮች፣ በጎዳናዎችና፣ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም