መንግስት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ትኩረት በመስጠቱ የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሬ አድጓል- ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ትኩረት በመስጠቱ የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሬ አድጓል- ኢንስቲትዩት
ባህር ዳር፣ግንቦት 13/2013 (ኢዜአ) መንግስት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ማሳደግ መቻሉን የኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ልማት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት አስታወቁ።
"ዘጠነኛው የጥጥ፣ የአልባሳትና የእሴት ሰንሰለት በአፍሪካ" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ኮንፈረንስ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ በኮንፈረንሱ መድረክ፤ እንዳሉት የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪውን በቀጣዮቹ 20 ዓመታት ለማዘመን መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በዚህም ከአስር ዓመት በፊት ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በዓመት ከ2 ሚሊዮን ዶላር በላይ የማይበልጥ የነበረው አሁን ላይ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህም ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪው አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ከተቻለ የማደግ አቅሙ ከፍተኛ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
ዘርፉ በሀገሪቱ ካለው ስነ ምህዳርና የሰለጠነ የሰው ሃይል አንጻር ሲታይ ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የበለጠ ለማደግ ምቹ ሁኔታዎች ያሉት መሆኑን አቶ ስለሺ ተናግረዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ምቹ ሁኔታዎችን ወደ ጥቅም በመለወጥ ለሀገሪቱ እድገትና ብልጽግ ለማዋል ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል አቅናጅቶ ማስኬድ ትኩረት የሚያሻው መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት ስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ ዘርፉን ለማሳደግ እየሰራ ነው፤ የተገኘውን ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲዎች ብቁ ተወዳዳሪ የሰው ሃይል በማፍራት ላይ አተኩረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪውን በእውቀት የመምራት ጥበብ እየተሻሻለ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር አበራ ከጪ ናቸው።
የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ብዙ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ዩኒቨርሲቲዎች በሚያፈሩት የሰለጠነ የሰው ሃይል ዘርፉን በእውቅት የመምራት ጥበብ እያደገ እንዲመጣ ማስቻሉን ተናግረዋል።
ዘርፉን ከእውቀት ጋር አጣምሮ የመምራት አዝማሚያ እያደገ በመምጣቱም ውጤታማ የሆኑ ኢንዱስትሪዎችን ማፍራት መቻሉን አስረድተዋል።
ኢንስቲትዩቱ እውቀትን ከክህሎት ጋር አጣምሮ የያዘ የሰው ሃብት በማፍራት ላይ ይገኛል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለጥጥ ምርት ምቹ የሆነ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ቢኖርም እስካሁን ማልማት የተቻለው ሶስት በመቶ በታች መሆኑ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም አሟጦ መጠቀም እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።
የጥጥ ልማትም ሆነ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ሰፊ የሰው ሃይል የሚጠይቅ በመሆኑ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት ባለፈ የስራ እድልን በመፍጠር ረገድ ተመራጭ የስራ ዘርፍ መሆኑን አመላክተዋል።
ሀገሪቱ ያላትን እምቅ ጸጋ ለእድገት ለማዋል መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው በበኩላቸው " የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪውን ሊያሳድግ በሚችል መልኩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የግል ሴክተሩና ኢንዱስትሪዎች አልተሳሰሩም" ብለዋል።
ሀገሪቱ ያላትን የሰው ሃብትና ሌሎች የዘርፉ ግብአቶች በአግባቡ ተጠቅሞ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪውን ውጤታማነት በዘላቂነት ለማሳደግ የባለ ድርሻ አካላት የተቀናጀ ስራ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግስትም በዘርፉ ያለውን እምቅ የመልማት አቅም በማሳደግ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና ለሀገር እድገት ለማዋል አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም አመልክተዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ኮንፍረንስ የባህር ዳር የኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የዘርፉ ምሁራን፣ የፌዴራልና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።