የውጭ ሃይሎች ጫናን በጋራ መከላከል እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ሃይሎች ጫናን በጋራ መከላከል እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13 /2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ በውጭ ሃይሎች የሚደርሱትን አሉታዊ ጫናዎች በጋራ መከላከል እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።
የሃይማኖት አባቶቹ ሕዝቡ ውስጣዊ የፖለቲካና ሌሎች ልዩነቶችን ወደኋላ በማድረግ በአገር ጉዳይ በአንድነት መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለአገሩ አምባሳደር ሆኖ እንዲሟገት ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼህ ቃሲም መሀመድ "ሕዝቡ በአገሩና በብሔራዊ ጥቅሙ ላይ ሊተባበር ይገባል" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የውጭ ኃይሎች በሕዳሴ ግድብና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ጫና ለማቃለል ሁሉም በጋራ መሥራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ቤተ-ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው የውጭ ተጽዕኖን ለማቃለል መፍትሄው በጋራ መቆም እንደሆነ ያስገነዝባሉ።
"በአገር ውስጥ ሠላምና አንድነት ካለ የውጭ ተጽዕኖ ይቀንሳል፤ በተቃራኒው ሕዝብ ከተከፋፈለና ሠላም ከሌለ ተጽዕኖው ይጨምራል" ብለዋል።
ስለዚህም ሕዝቡ በግድቡም ይሁን በሌሎች ጉዳዮች ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስከብር መልኩ በትብብርና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያዊያን በውስጥ ጉዳዮች ያሏቸውን ልዩነቶች ያለማንም ጣልቃ ገብነት በሠላማዊ መንገድ መፍታትና ለጋራ ጉዳይ በጋራ መቆም እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ተሾመ አመኑ የሚሰነዘሩትን ጫናዎች በኅብረት መመከት እንደሚቻል ነው የጠቀሱት።
"ግድቡን በተመለከተ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትክክለኛ መረጃ በማስተላለፍ ረገድ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ድርሻ አለብን" ብለዋል።
የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ጭምር የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ መገንባትና አሉታዊ ጫናዎችን መከላከል እንደሚገባም ተናግረዋል።
በተለይም ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ ጠቃሚ መረጃዎችን ማስተላለፍና ለአገር ጥቅም መሟገት ተገቢ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።