በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶች ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶች ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ
ሀዋሳ፤ ግንቦት 13/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ተባብረው ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ ፡፡
በዘላቂ ሀገራዊ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ላይ ያተኮረው ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባኤ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው ፡፡
በጉባኤው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ ፣ ህዋ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አታላይ አየለ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ እያደገ ከመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ቀጣይነት ያለው ልማት በማምጣት የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሀገሪቱ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል።
ይህም በዕውቀት ፣ በትምህርትና ሳይንስ በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ለዚህም የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብቶች መቃኘት ፣ መመርመርና ከጉዳት ሥጋት ነፃ በሆነ መንገድ ማልማት የሚቻልበትን መንገድ ማጥናት ብሎም ከፖሊሲ አውጭዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል ፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት ይህን ቅድመ ሁኔታ ያሟላ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ፕሮፌሰር አታላይ እንዳሉት፤ ግድቡ የሚገነባበት ቦታ ከእሳተ ገሞራ ሥጋትና በዚህ ምክንያት በግድቡ ላይ ሊመጣ ከሚችል አደጋ ነፃ መሆኑ ለኢትዮጵያም ሆነ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ዘላቂ እፎይታን የሚሰጥ ሲሆን በወቅቱ በጥናቱ የተሳተፉ ምሁራን የአስፈፃሚ አካላት ትብብር ውጤት ነው ፡፡
ሆኖም የህዳሴውን ግድብም ሆነ ሌሎች ግድቦችና ሀይቆችን በዘላቂነት ለመጠቀም ኮረብታማ ቦታዎች ላይ የአፈርና ውሀ ጥበቃ እንዲሁም የደን ልማት ሥራዎችን በማከናወን ጎርፍና ደለልን መከላከል እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ረገድ በየአካባቢው ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥናትና ምርምሮችን ከማካሄድ ባለፈ ከፖሊሲ አውጪዎችና ከሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብረው ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በገፀም ሆነ ከርሰ ምድር የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች ናት ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምድር ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ይርጉ ናቸው።
በከርሰ ምድር ብቻ ሀገሪቱ ካሏት የነዳጅና ማዕድናት ባሻገር በተፈጥሮ አቀማመጧ ሰፊ የሆነ የጂኦ ተርማል ኃይል እምቅ ሀብት እንዳላት ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎቿ እስከ 10 ሺህ ሜጋ ዋት ድረስ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል እምቅ የጂኦ ተርማል ኃይል ሀብት እንዳላት ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተወሰኑ አካባቢዎች ይህን ኃይል ጥቅም ላይ ለማዋል የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን አስታውሰው በስፋት ተጠንተው በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ከቻልን የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል ፡፡
ሌሎችንም ሀብቶችን በጥናት ለይቶ ፣ ጠብቆና አልምቶ ለመጠቀም ደግሞ እውቀቱ ያላቸው ምሁራንና አስፈፃሚ አካላት ማዶ ለማዶ መተያየትን በማስወገድ ተቀራርበውና ተባብረው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ኮምፒቲሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዘይቱ ጋሻው በበኩላቸው፤ የጉባኤው ዓላማ በምሁራን መካከል የእውቀትና የአዳዲስ ግኝቶች ሽግግር እንዲኖር ብሎም አስፈጻሚ አካላት እነዚህን ግኝቶች ተግባር ላይ ለማዋል የሚያስችላቸውን ግንዛቤ እንዲጨብጡ ለማመቻቸት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኮሌጁ በአካባቢው የሀዋሳ ሀይቅን ከደለል ፣ ብክለትና በውስጡ ያለውን ብዝሀ-ሕይወት ከጉዳት ለመታደግ ከኢንዱስትሪዎች ፣ ከመንግሰት አካላትና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር በርካታ ስራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
ዶክተር ዘይቱ እንዳመለከቱት፤ በሀይቁ ውስጥ ያሉ ዓሳዎችን ወቅቱን ካልጠበቀና ከአቅም በላይ ከሆነ የማስገር ተግባር ለመታደግም ለአካባቢው ማህበረሰብ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እየሰሩ ነው ፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ አማራጭ የምርት ምንጭ እንዲኖረውም ማሳ ውስጥ በኩሬ አሣ የማምረት ቴክኖሌጂን በማላመድና የዓሣ ጫጩቶችን በማቅረብ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤው ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡