በኢትዮጵያ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት የአረንጓዴ አሻራ ትግበራን የተመለከተ ገለጻ ተደረገ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2013(ኢዜአ) የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የ2013 የአረንጓዴ አሻራ ትግበራን አስመልክተው በኢትዮጵያ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ገለጻ አደረጉ።

ሚኒስትሩ በገለጻቸው የአረጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ፋይዳና አተገባበርን በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አማካኝነት ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም አካባቢ ጥበቃ ያላትን ቁርጠኛ አቋምም ገልጸዋል።

የገለጻው ዓላማ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ የመርሃ-ግብሩን ሁለንተናዊ ፋይዳና ሂደት ተገንዝቦ ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ማድረግ መሆኑም ተጠቁሟል።

ከሁለት ዓመታት በፊት የተጀመረው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዘንድሮም "ኢትዮጵያን እናልብሳት" በሚል መርህ ይተገበራል። 

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 7 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ነው የታቀደው።

ከዚህ ውስጥ 1 ቢሊዮን ችግኞች ለጎረቤት አገራት የሚቀርቡ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ጎን ለጎን በጋራ የመልማት እቅድን ለማገዝ የድርሻዋን ለመወጣት ያለመ ነው።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአጠቃላይ ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም