ቀጥታ፡

ምርጫው ለአፍሪካ አገሮች ተምሳሌት እንዲሆን በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

ጎንደር፣ ግንቦት 13 /2013 (ኢዜአ) 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊነቱ ተጠብቆ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰረት እንዲጥልና ለአፍሪካ ሃገራት ተምሳሌት እንዲሆን ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ገለጹ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ "6ኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቅድመና በድህረ ምርጫ ወቅት የአጋር አካላት ተሳትፎና ሚና'' በሚል መርህ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የታደሙት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንደተናገሩት፤ በአገረ መንግስት ግንባታ የመንግስት ቅቡልነትንና የተቋማትን ብቃት በማሳደግ ሂደት ውስጥ ምርጫ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው።

ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካ ነጻነት ተምሳሌት መሆናቸውን አስታውሰው፤ ይህ ተምሳሌት በምርጫው መደገም አንዳለበት ገልጸዋል።

"በምርጫው ለውጭ ሃይል የማይላላክ ጠንካራ መንግስት ፈጥረን ዳግመኛ ተምሳሌነታችንን ልናረጋግጥ ይገባል'' ብለዋል።

የውጭ ሃይሎችን ሴራ በማክሸፍ ኢትዮጵያን ዳግም ከፍ ለማድረግ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትና መጪው ምርጫ በስኬት መጠናቀቅ እንደሚኖርበት ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ በጋራ መቆም ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች አገርና ህዝብን ከአደጋ መታደግን የህልውና ጉዳይ አድርገው በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የህዝብ አንድነትን ለማጠናከር ዩኒቨርሲቲዎች ህዝብን የማንቃትና የማሳወቅ ማህበራዊ ግዴታቸውን ሊተገብሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው ''ወደ ዴሞክራሲ በሚደረግ ጉዞ ውስጥ የተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና የዜጎች ንቁ ፖለቲካዊ ተሳትፎ መሰረታዊ ነው'' ብለዋል።

"ምርጫውን ነጻና ፍትሀዊ በማድረግ የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን በመጨረስ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ የሚገቡ ሃይሎችን ልናሳፍራቸው ይገባል'' ብለዋል፡፡

ዜጎች በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ዩኒቨርሲቲው በምሁራን የታገዙ የክርክር መድረኮችን በማመቻቸት ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

"አንድ ምርጫ የተሟላ የሚሆነው የምርጫው ሂደት መገለጫ የሆኑት ዴሞክራሲዊነት፣ ነጻነትና ፍትሃዊነት ሲረጋገጡ ነው" ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ናቸው።

"ምርጫ የመንግስት ቅቡልነት ማረጋጋጫ መሳሪያ ነው፤ የህዝብ ቅቡልነትን ለማግኘት ደግሞ ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች እኩል እድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለፉት ምርጫዎች ተጨባጭ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም የቅድመና ድህረ ምርጫ ሂደቶች አዎንታዊና አሉታዊ ውጤቶች በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች በዩኒቨርስቲው የህግ ትምህርት ቤት የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሁፎች በመድረኩ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም