የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የምሁራን ውይይት ሊያካሂድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የምሁራን ውይይት ሊያካሂድ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13/2013/ኢዜአ/ ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ዕውቀትና ማስረጃን መሰረት ያደረገ እንዲሆን የሚያግዝ የምሁራን ውይይት በቀጣይ ሳምንት እንደሚያካሂድ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አስታወቀ።
የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ለኢዜአ እንደተናገሩት ውይይቱ ከታሪክ፣ ከህግና ከፖለቲካ አንጻር ለምርጫ የሚረዱ ምሁራዊ ምክረ ሃሳቦችን ለመስጠት የተዘጋጀ ነው።
በውይይቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያገለግሉ የታሪክ፣ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት እንዲሁም የህግ ምሁራን ከምርጫው ጋር ግንኙነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ጽሁፍ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ምርጫ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ዳሰሳ፣ መጪው ምርጫ ለሰላምና መረጋጋት ያለው እንድምታና ምርጫና ሰላም የተቋማትና የህግ ሚና በሚሉ ርዕሶች ጹሁፍ በማቅረብ ትንታኔ ይሰጣሉ።
ምርጫ የአገርን ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስን ሂደት በመሆኑ ዜጎች ነጻና ገለልተኛ ሆነው መምረጥ እንዲችሉ ከህግ አግባብ ያለውን ሁኔታ ምሁራኑ ያስረዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
በተጠቀሱት ርዕሶች ላይ የሚመክረውን የምሁራን የውይይት መድረክ በቀጣይ ሳምንት ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ውይይቱ በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መራጩ ህዝብና አስፈጻሚ ተቋማት ምርጫ ከታሪክ፣ ከህግና ከፖለቲካ አንጻር ያላቸው ግንኙነት ላይ ግንዛቤን ለመጨመር ይረዳል ብለዋል።
ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ እውቀትና ማስረጃን መሰረት አድርጎ እንዲካሄድ ምሁራን በአገራቸው ጉዳይ ሙያዊ ምክረ ሃሳብ ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል።
አካዳሚው ውይይቱን ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ ለማካሄድ ማቀዱን ገልጸው በቀጣይ ሳምንት የሚካሄደው በቅድመ ምርጫ ወቅት የታቀደው እንደሆነ ገልጸዋል።
ውይይቱ በበየነ መረብ በመታገዝ ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን በአገር ውስጥና በተለያዩ የአለም አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን እንዲሁም ለኢትዮጵያ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የውጭ አገር ዜጎች ባሉበት ሆነው ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እውቀትና ማስረጃ ላይ የተመሰረተ የምርምር ሃሳቦችን ለህዝብና ለመንግስት ፖሊሲ ግብአት የሚውሉ ሃሳቦችን የሚያቀርብ ከዘጠኝ አመታት በፊት የተቋቋመ የምሁራን ስብስብ ነው።
በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ እያስተዋወቁ ሲሆን ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የድምጽ መስጫ ቀን መሆኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ ይታወሳል።