ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጭ ጣልቃ ገብነት መመከት የሚቻለው ሠላምና አንድነትን በመጠበቅ መሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13 /2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጭ ጣልቃ ገብነት መመከት የሚቻለው ሠላምና አንድነትን በመጠበቅ እንደሆነ ተገለጸ።

ኢዜአ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳይ በሚመለከት ከአርቲስት አስገኘሁ አሸኮ /አስጌ ዴንዳሾ/፣ ከእግር ኳስ ተጫዋች ጌታነህ ከበደ እና የብሔራዊ ቡድንና የቡና ክለብ አስጨፋሪ አዳነ ሽጉጤ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አስተያየት ሰጪዎቹ ዜጎች ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን አስጠብቀው ለአገር ሠላም የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ከውጭ የሚደረጉ ጫናዎች ጎልተው መውጣታቸውን ጠቅሰው፤ ይህን ጫና መመከት የሚቻለው ሕዝቡ አንድነቱን ሲጠብቅ እንደሆነ ተናግረዋል።

አርቲስት አስገኘሁ /አስጌ ዴንዳሾ/ ኢትዮጵያዊያን በተለይም ወጣቶች ከብሽሽቅ ፖለቲካ ወጥተው አንድነት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ተናግሯል።

ውስጣዊ መከፋፈል ከሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ውጫዊ ጫና በር እንደሚከፍት ገልጾ፤ "ዜጎች ለሠላም ዘብ መቆም አለባቸው፤ መንግስትም ሠላም የማስፈን ሃላፊነቱን መወጣት አለበት" ብሏል።

የአገር ሰላም እንዲደፈርስ እርስ በርስ ለማጋጨት የሚሰሩ ሃይሎች ላይ መንቃት እንደሚያስፈልግ 'አስጌ ዴንዳሾ' አስገንዝቧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የቡና ክለብ አስጨፋሪ አዳነ ሽጉጤ ሠላም ማስፈን የሚቻለው ዜጎች አንድነታቸውን መጠበቅ ሲችሉ መሆኑን ይገልጻል።

ለሠላም መስፈን ዋነኞቹ ባለድርሻዎች ዜጎች መሆናቸውን በመጠቆም።

ኢትዮጵያዊያን ሰንደቅ ዓላማቸውን በማስቀደም አንድነታቸውን እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርቧል።

"ሠላም ለማምጣት ደግሞ አንድነት ያስፈልጋል፤ አንድነት ካለ ሠላም የማይመጣበት ምክንያት የለም" ብሏል።

ከውጭ የሚመጡ ማናቸውንም አይነት ጫናዎች በጋራ መከላከል ይገባል ያለው ደግሞ የብሔራዊ ቡድንና ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ክለብ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ጌታነህ ከበደ ነው።

"የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት የሚከናወንበት ጊዜ በመቃረቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሠላምና አንድነታችንን መጠበቅ ይገባል" ብሏል።

"ከውጭ የሚመጣ ሃይል እኛን ለመበታተን ይፈልጋል" ያለው ጌታነህ፤ በአንድነት ኢትዮጵያን ሰላም ማድረግ እንደሚቻል እምነቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም