ቀጥታ፡

ባህርዳር ከተማን ጥራት ባለው መዋቅራዊ ፕላን በመምራት ተወዳዳሪ ከተማ ለማድረግ እየተሰራ ነው-አስተዳደሩ

ባህርዳር፣ ግንቦት 13/ 2013 (ኢዜአ) የባህርዳርን ጥራት ባለው መዋቅራዊ ፕላንና በብቁ አመራር በመምራት እድገቷን ለማስቀጠልና ተወዳዳሪ ከተማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስተዳደሩ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ባሰራው መዋቅራዊ ፕላን ላይ ከከተማዋ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ለመወያየት ያዘጋጀው የሁለት ቀን መድረክ ዛሬ ተጀምሯል ።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዬ አለባቸው በወቅቱ እንደገለጹት የከተማውን እድገት ለማስቀጠልና ተወዳዳሪ ለማድረግ አዲስ መዋቅራዊ ፕላን ተዘጋጅቷል ።

በመዋቅራዊ ፕላኑ የከተማዋን ጸጋዎች ለመጠበቅና ለመንከባከብ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።

"በከተማዋ ላይ የተስፋፋውን ህገ ወጥ ግንባታ፣ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ እንዲሁም የአካባቢ ብክለትና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ ፕላኑን ማዘጋጀት አስፈልጓል" ብለዋል።

"መዋቅራዊ ፕላኑን ወደ መሬት ለማውረድ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በመዋቅራዊ ፕላኑ ላይ ህዝቡ ተመካክሮና ተወያይቶ የራሱን ግብዓት በመጨመር ለተፈጻሚነቱ የባለቤትነት መንፈስ እንዲዳብር ለማድረግ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል ።

የባህርዳር መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር መንግስቴ አባተ በበኩላቸው መዋቅራዊ ፕላኑን ለመስራት ከ90 በላይ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ የመሰረተ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ፣ የቅየሳ፣ ካርታ ስራና የመሬት አስተዳደር ቡድኖች ተዋቅረው ከየሙያ ዘርፋቸው ለመዋቅራዊ ፕላኑ ስኬት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ፕላኑ የአባይ ወንዝና ጣና ሃይቅን የመሰሉ የብዝሃ ህይወት አካላትን፣ ቅርሶችን፣ የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤና ሌሎች የከተማዋ ጸጋዎች ተብለው የተለዩን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ትኩረት የሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

"መዋቅራዊ ፕላኑን ወደ መሬት አውርዶ በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ ከተማዋ በ10 ዓመት ጊዜ ከሀገሪቱ ከተሞች ተወዳዳሪ ትሆናለች" ብለዋል ።

“መዋቅራዊ ፕላኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ የዘላቂ የከተማ ልማት ምሰሶዎችን በማካተት የተከናወነ ነው” ያሉት ደግሞ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ጌታቸው ይርጋ ናቸው።

"ከኢኮኖሚክስ አንጻር ሲታይ በፕላኑ እስካሁን ያልነበሩ የዝቅተኛ፣ የመካከለኛና የትላልቅ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ሌሎች ለከተማ እድገት የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች ተካተዋል" ብለዋል።

ፕላኑ በከተማዋ ሁሉም መግቢያ በሮች የአርሶ አደሮች መገበያያ፣ ዘመናዊ ሱፐር ማርኬቶችና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚገነቡበት ቦታ ያለው መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

እንደ ዶክተሩ ገለጻ ፕላኑ በከተማዋ መሃል የሚስተዋለውን መጨናነቅ በማስቀረት ለነዋሪዎቿና ለጎብኝዎች ምቹና ተወዳዳሪ እንድትሆን ያስችላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም