የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚካሄደውን የውጭ ጣልቃ ገብነት አወገዘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚካሄደውን የውጭ ጣልቃ ገብነት አወገዘ
ግንቦት 13 /2013 (ኢዜአ) መሠረቱን በአሜሪካ ያደረገው የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚካሄደውን የውጭ ጣልቃ ገብነት አወገዘ።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ ወይም አንድ ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት በውጤቱ ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር የሚሞክሩ ሁሉም የውጭ ኃይሎችን እንደሚያወግዝ ነው ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በላከው ደብዳቤ የገለጸው።
ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት የዴሞክራሲ ምሰሶዎች አንዱ የሆነውን ግልጽ ምርጫ ለማካሄድ ገለልተኛ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ማቋቋም መሆኑን አውስቷል።
ይህም ለዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ሽግግር አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን ነው ያመለከተው።
“የምርጫ ሂደት ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ ወይም አንድ ድምፅ ከመስጠቱ በፊት በውጤቱ ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር የሚሞክሩ ሁሉንም የውጭ ኃይሎችን አጥብቀን እናወግዛለን” ብሏል።
“የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ ጉዳዮች የሰጠውን ትኩረት እያደነቅን በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ላይ አላስፈላጊ የሆነ ጣልቃ ገብነት ግን የሚያስከተለው አደጋ ያሳስበናል” ያለው ምክር ቤቱ፤ በኢትዮጵያ የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመን ጥቃት ተከትሎ እንደሆነ አስገንዝቧል።
የትኛውም ሉዐላዊ አገር እንዲህ አይነት ክህደት ሲፈጸምበት ሊወስደው የሚችለውን እርምጃ የኢትዮጵያ መንግስት መውሰዱን በማመልከት፤ “የኢትዮጵያ መንግስት የአገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ሊደገፍ ይገባል” ብሏል።
“ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከኢትዮጵያ ጋር የምትሰራው አሜሪካ ኢትዮጵያንና ቀጠናውን ለማተራመስ የሚሰራውን የህወሓት የሽብር ቡድን ደጋፊዎችና የውጭ ተባባሪ ድርጅቶችን መከታተል ይኖርባታል” ሲል አስገንዝቧል።
“አሜሪካ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ፣ ለሁለተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ድጋፍ እንደምትሰጥና በኢትዮ-ሱዳን መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ በውይይት እንዲፈታ እንዲሁም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚካሄደው የመልሶ ግንባታና የሰብአዊ ድጋፍን በማገዝ አሜሪካ ገንቢ ሚና እንደምትጫወት እምነታችን ነው” ብሏል።
ምክር ቤቱ “ከ115 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውና በፕሬዚዳንት ቴዲ ሩዝቬልት የመሪነት ዘመን የተጀመረው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ጠንካራ ወዳጅነት እና የረጅም ጊዜ አጋርነት በጋራ ብልጽግና ወደፊት እንደሚራመድ እናምናለንም” ሲል ገልጿል።