የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ የሚደረገው ዝግጅት በመገባደድ ላይ ነው - ምርጫ ቦርድ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ የሚደረገው ዝግጅት በመገባደድ ላይ ነው - ምርጫ ቦርድ
አዲስ አበባ ግንቦት 13/2013/ኢዜአ/ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ አብዛኛው የዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ሕዝበ ውሳኔው አጠቃላይ ምርጫው ከሚካሄድበት ቀን ጋር አንድ ላይ እንደሚካሄድ ገልጿል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤንች ሸኮ ዞን፣ የዳውሮ ዞን፣ ሸካ ዞንና የካፋ ዞን እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ በተናጥል በየምክር ቤቶቻቸው መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሔዱት መደበኛ ጉባኤ "ደቡብ ምዕራብ ህዝቦች" ክልልነት ለመደራጀት የቀረበውን ሀሳብ በሙሉ ድምጽ ማጽደቃቸው የሚታወስ ነው።
የዞኖቹ እና የልዩ ወረዳው ምክር ቤቶች የወሰኑት ውሳኔ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት አቅርበው ምክር ቤቱ ደግሞ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መምራቱ ይታወቃል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትም መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ጥያቄውን ተቀብሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ ወስኗል።
የቦርዱ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሶልያና ሺመልስ ከምክር ቤቱ ውሳኔ በኋላ የተለያዩ የዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ቦርዱ ሕዝበ ውሳኔውን የሚካሄድበትን ቀን ከስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ከሚካሄድበት ቀን አንድ ላይ እንዲሆን ማድረጉንና ለሕዝበ ውሳኔው የሚያስፈልግ የበጀት ዝግጅት ማድረጉንም ተናግረዋል።
ሕዝበ ውሳኔውና አጠቃላይ ምርጫውና አንድ ላይ መካሄዳቸው ወጪን በከፍተኛ መጠን እንደሚቀንስ አመልክተዋል።
ለአጠቃላይ ምርጫውና ለሕዝበ ውሳኔው አንድ የምርጫ መዝገብ መዘጋጀቱን ገልጸው መራጮች ለምርጫውም ለሕዝበ ውሳኔውም አንድ ላይ ድምጽ ይሰጣሉ ብለዋል።
በዞኖቹና በልዩ ወረዳው ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የተመዘገቡ ሰዎች ለሕዝበ ውሳኔው እንደተመዘገቡ የሚቆጠር በመሆኑ ለሕዝበ ውሳኔው የሚሳተፉ ሰዎች ምዝገባ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ባለው አሰራር መሰረት ለምርጫውና ለሕዝበ ውሳኔው የድምጽ መስጫ ወረቀት ተዘጋጅቶላቸው ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ነው የገለጹት።
ለሕዝበ ውሳኔው የተዘጋጀው የድምጽ መስጫ ወረቀት በህትመት ላይ እንደሚገኝና ለስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የታተመው የድምጽ መስጫ ወረቀት በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰራጨት ሲጀመር ወደ ዞኖቹና ወደ ልዩ ወረዳው በሚገኙ የምርጫ ክልሎች በልዩ ሁኔታ እንደሚላክ ነው ወይዘሪት ሶልያና ያስረዱት።
ለድምጽ መስጫ ሳጥን፣ ለአስፈጻሚዎች ስልጠና፣ ለፕሮጀክት ስራዎች ወጪና ተጓዳኝ ጉዳዮች ተጨማሪ በጀት የሚያስፈልግ በመሆኑ ምርጫ ቦርድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ76 ሚሊዮን ብር ገደማ ጥያቄ አቅርቦ ምላሹን እየተጠባበቀ ይገኛል ብለዋል።
ለሕዝበ ውሳኔው የሚያስፈልገውን ምልክት በሚያዚያ ወር ይፋ ማድረጉንም አስታወሰዋል።
የተያያዙ እጆች የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ ዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን ከደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል መመስረታቸውን እደግፋለሁ የሚለውን እንደሚወክል ገልጸዋል።
እንዲሁም የጎጆ ቤት የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ ዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን ከደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል አካል ሆነው መቀጠላቸውን እደግፋለሁ የሚለውን ይወክላል ብለዋል።
ምርጫ ቦርድ ለሕዝበ ውሳኔው ልዩ ቡድን ማዋቀሩንና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕዝበ ውሳኔውን ለማስተባበር ካቋቋመው ፕሮጀክት ቢሮ ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶ ቦርዱ እስካሁን ምንም አይነት አቤቱታ እንዳልደረሰውም ነው ወይዘሪት ሶልያና ያስረዱት።
ለሕዝበ ውሳኔው የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ለአጠቃላይ ምርጫው የተመዘገቡ ሰዎች አሃዝ ተጠቃሎ ሲመጣ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የሚካሄድበት ቀን ወደ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲራዘም በመደረጉ ሕዝበ ውሳኔው በምርጫው ቀን እንደሚከናወን አመልክተዋል።