ሰላሟ የተጠበቀና አረንጓዴ ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ሰላሟ የተጠበቀና አረንጓዴ ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ግንቦት 13/2013 ሰላሟ የተጠበቀና አረንጓዴ የለበሰች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑ ተገለጸ።
የአረንጓዴ ልማት መርሃ-ግብር ላይ የተሳተፉ አርቲስቶችና ስፖርተኞች ለስኬቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑን አውቆ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን በመድረኩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አረንጓዴ ልማትን አስመልክቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደው መርሃ-ግብር ላይ ታዋቂ የጥበብ ሰዎችና የስፖርት ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ላይ ማብራሪያ ያቀረቡት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን ለማስቀጠል ቃል ገብተው በተግባር እያሳዩ ካሉ ውስን አገራት መካከል እንደምትጠቀስ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን መልከዓ ምድርና አየር ንብረት መልካም አጋጣሚና የህዝቦቿና አንድነት በመጠቀም አሁንም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ አሁን በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የአረንጓዴ ልማት ተሳትፎ ለማስቀጠልና አሻራዋን ለማስቀመጥ ጎረቤት አገራትን ጭምር በመርሃ-ግብሩ እንዲሳተፉ በማነሳሳትና ችግኝ አዘጋጅቶ በመስጠት ሰፊ ስራ ለመስራት ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀች ገልፀዋል።
ባለፉት ሁለት አመታት የተሰራው የአረንጓዴ ልማት ስራ ትልቅ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ በተለይ አርቲስቶችና አትሌቶች ማህበረሰቡን በማነሳሳትና ራሳቸውም በቀጥታ በመሳተፍ ሚናቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመርሃ-ግብሩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ፕሮግራሙ አገርን ለትውልድ ማስተላለፍን አላማ ያነገበና ሁሉም ሊሳተፍበት የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት ከተከላ እስከ መንከባከብ ድረስ ሁሉም ዜጋ እንዲሳተፍ በማድረግና ራሳቸውም በቀጥታ በመሳተፍ ለመርሃ-ግብሩ መሳካት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
ይህ የአረንጓዴ ልማት አሻራ ፕሮግራም ከፖለቲካና ከሌሎች አመለካከቶች የፀዳ መሆኑን ገልጸው ሁሉም ሊሳተፍበት ይገባል ብለዋል።
መርሃ ግብሩ ከኢትዮጵያዊያን አንድነትና ከህዳሴው ግድብ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ መሆኑ ደግሞ የበለጠ የሚያነሳሳ መሆኑን ነው የጠቀሱት።