ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን ከህዝብ ፍላጎት ተነስተው የሚሰሩ ተቋማት መሆን አለባቸው - ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል

ግንቦት 12 /2013 (ኢዜአ) "መገናኛ ብዙኃን ከህዝብ ፍላጎት ተነስተው የሚሰሩ ተቋማት መሆን አለባቸው" ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል አስገነዘቡ።

መገናኛ ብዙኃን ስለ ሰላም የህዝቦች አብሮነት እና የሀገር ግንባታ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን "መገናኛ ብዙኃን ለአብሮነት እና አገር ግንባታ" በሚል መሪ ሐሳብ እያካሄደ ባለው ውይይት ላይ የተገኙት ሚኒስትሯ፤ "መገናኛ ብዙኃን አንድነትን በሚያጠናክሩና ሰላምን በሚያሰፍኑ ሥራዎች ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል።

መገናኛ ብዙኃንን በአግባቡ አለመጠቀም አገርን እስከ ማፍረስ ሊደርስ የሚችል አደጋ እንደሚያመጣም ጠቁመዋል።

መገናኛ ብዙሃን ከህብረተሰብ ጥቅም በተጻራሪ መቆም እንደሌለባቸው ገልጸው፤ "ህዝብ ምን ይፈልጋል? ምን ጎድሎታል? ምን አለው ምን የለውም? ከሚለው የሚነሱ ተቋማት መሆን አለባቸው" ብለዋል።

በመሆኑም መገናኛ ብዙሃኑ ከህዝብ ፍላጎት ተነስተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበው፤ "ሰላም የህዝባችን ፍላጎት ነው አይደለም? አብሮነት የህዝባችን ፍላጎት ነው አይደለም? አገር የሚባለው ጉዳይ የጋራ ፍላጎት ነው አይደለም? የሚሉ ጉዳዮችን ማየት ይጠይቃል" ብለዋል።

ስለዚህ ሰላም ማረጋገጥ፣ አብሮነትና አገር ግንባታ ላይ መስራት የመገናኛ ብዙሃኑ የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንደሚገባው ጠቁመዋል።

አገር እና ህዝብ ከሌለ ምንም ነገር መኖር አይችልምና መገናኛ ብዙኃን ይህንን ታሳቢ አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"አሁን ባለንበት ወቅት ደግሞ አገራዊ አንድነት እና ህዝብን የሚያቀራርቡ ሥራዎችን በስፋት ማከናወንን ይጠይቃል" ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ መንግሥት ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ትልቅ አቅም አላቸው ብሎ ከለያቸው የሙያ መስኮች መካከል አንዱ መገናኛ ብዙኃን መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው "መገናኛ ብዙኃን ድምጽ ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድምጽ በመሆን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስብራቶችን በመጠገን የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል መሥራት አለባቸው" ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መገናኛ ብዙኃን ለአገር አንድነትና ለህዝብ ወገንተኝነታቸውን በማሳየት የሙያ ስነ-ምግባርን ጠብቀው መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የህዝብ ወገንተኝነት ያላቸውን መገናኛ ብዙሃን ለመፍጠር መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በመገናኛ ብዙሃኑ የሚቀረጹ አጀንዳዎች ማህበራዊ ሃላፊነትን ለመወጣት በሚያስችል መልኩ ሊሆን እንደሚገባም ገልጸዋል።

የህዝብ ፍላጎትንና የመገናኛ ብዙሃንን ጥቅም አጣጥሞ ማስኬድ ተገቢ እንደሆነ የገለጹት የመድረኩ ተሳታፊዎች፤ መብትና ግዴታን የለየ ተቋም መፍጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም